
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን የሚጠብቀው ተስፈኛው ወጣት፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ የተለያዩ ሙያዎችን ከወላጆቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸውና
ከአካባቢያቸው ይማራሉ፡፡ ምናልባትም የወደፊቱ ዕጣ ፋንታቸው በልጅነት በሚያሳዩት ዝንባሌ የሆኑም ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡
የዛሬው ባለታሪካችን ከልጅነት የዕቃቃ ጨዋታ ጀምሮ የተለያዩ ቁሶችን የመገጣጠም ክህሎት የነበረው ግለሰብ ነው፡፡
ወጣት አቤል ጫኔ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በልጅነቱ የነበረው ፍላጎት እና ምኞት እንደሆነ ይናገራል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ
ነዋሪ የኾነው ወጣት አቤል “ከልጅነቴ ጀምሮ የሽቦ መኪና እገጣጥም ነበር፤ የራሴን አጠናቅቄ የጓደኞቼንም እሠራ ነበር”
ብሎናል፡፡ ወጣት አቤል አባቱ በባሕር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በጥገና ሥራ ተመድበው የሚሠሩትን ሥራ በልጅነት ዐዕምሮ
ይቀስም እንደነበረ ነግሮናል፡፡
ወጣቱ ለሥራ ሲደርስም የግል የጥገና ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሶ የጥገና ሙያውን የበለጠ ለማሳደግ ባሕር ዳር
ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በመግባት በአዉቶ ኢንጂን በደረጃ 2 እንዲሁም በጀኔራል ፋብሪኬሽን በደረጃ 3 በ2007 ዓ.ም ማጠናቀቁን
አስረድቷል፡፡ በ2002 ዓ.ም ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር 3 ሺህ ካሬሜትር የኢንቨስትመንት ቦታ በመረከብ በሀገር በቀል
ክህሎት ጀልባዎችን እያመረተ እደኾነም ነግሮናል፡፡
ቀደም ብሎ በአካባቢው የሚገኙትን ጀልባዎች ሲጠግን የነበረው ወጣቱ ዛሬ “አቤል ጫኔ የጀልባ ማምረትና ጥገና” በሚል የሥራ
ፈቃድ በማውጣት ጀልባዎችን እያመረተና እየጠገነ ለአካባቢው የውኃ ትራንስፖርት ዕድገት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ወጣት አቤል ካገለገሉ ተሽከርካሪዎች አለያም አዲስ ሞተር ከውጪ በማስገባት ነው ጀልባዎችን እያመረተ የሚገኘው፡፡
ለሥራው ስኬታማነት ወደ ሆላንድና ጀርመን በማቅናት ሙያውን ለማዳበር ጥረት ማድረጉን አስረድቷል፡፡ “በተለያየ ምክንያት
የተበላሹ ተሽከርካሪዎችን፣ ጉልበት ያላቸው ሞተሮችን በመውሰድና ከፍተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸውን አዳዲስ ሞተሮችን ከውጪ
በማስገባት ጀልባዎችን በባሕር ዳር ከተማ እያመረትኩ ነው” ብሏል፡፡ በሚያመርተው ጀልባ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ
እየሆነ እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡
ወጣት አቤል በተለይ ለ”ደቅ” ማኅበረሰብ ጀልባዎችን በዱቤ በመሸጥ ለችግሮቻቸው እንደደረሰላቸው ተናግሯል፡፡ “የ’ደቅ’
ማኅበረሰብ ህክምና ቢያስፈልጋቸው ለጀልባው ነዳጅ ብቻ በመሙላት ወደሚፈልጉት የሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋም መሄድ
ይችላሉ” ብሏል፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ በጀልባ ትራንስፖርት የተሰማሩ ሰዎች ስለጀልባቸው ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራቸው ሥልጠና
ለመሥጠት ማሰቡንም ጠቁሟል፡፡
በጀልባ ትራንስፖርት የተሰማሩ ሰዎች ሐይቁ ላይ ሆነው ጀልባቸው ብልሽት ቢያጋጥመው እንዴት አድረገው መጠገን
እንዳለባቸውና በሐይቁ ላይ አደጋ ቢከሰት ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ለማሰልጠን ማቀዱንም ተናግሯል፡፡ ወጣት አቤል
በዋነኝነት የጀልባ ማምረት ሥራ ቢሠራም ሌሎች የግንባታ ቁሳቁስ እንደሚያመርትም ተናግሯል፡፡
ወጣቱ በጀልባ ሥራና በግንባታ ቁሳቁስ ማምረት ብቻ ሳይሆን የጣና ሐይቅ ሥነ-ምህዳርን በማስዋብና በመጠበቅ
የተምሣሌትነት ሥራን እየሠራ ይገኛል፡፡ በሐይቁ ዳርቻ የድንጋይ ካብ በመካብ፣ ድልድይ በመገንባት፣ ለአሳዎች ምቹ ሁኔታን
በመፍጠርና በመመገብ እየተመናመነ የመጣውን የአሳ ዝርያ እየታደገ መኾኑንም ጠቁሟል፡፡ አሳዎች ተመግበውና ተራብተው
መልሰው ወደ ሐይቁ እንዲገቡ በማድረግ ለሌሎች አርአያ መሆን ችሏል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ጀልባዎችን ማምረት ዕቅዱ እንደሆነም
ወጣት አቤል ገልጻል፡፡
አሁን ላይ ለ13 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደፈጠረላቸው የተናገረው ወጣቱ ወደፊት ለ40 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር
እንዳቀደም አስረድቷል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር መንገድን ጨምሮ የተለያዩ የመሠረተ ልማቶችን እንዲያሟላለት
መጠየቁንም ተናግሯል፡፡
ወጣት አቤልን በሥራ ከሚያውቁት ውስጥ የባሕር ዳር አሳና ሌሎች የውኃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና
ተመራማሪ አቶ ደረጄ ተዋበ አንዱ ናቸው። አቤል ታታሪና ቴክኖሎጂን በቀላሉ መቀበል የሚችል አቅም ያለው ወጣት ነው
ብለዋል። ጀልባ በራሱ እጅ በማምረት የሚታወቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በርካታ ግልጋሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ነግረውናል።
“አቤል በአሳ ዘርፍ ወደ ውጭ ሄዶ በመሰልጠኑ የአሳ ምርምር ዘርፍን እየደገፈ ነው” ብለዋል። ጀልባ ሲበላሽ በመጠገንም
ይታወቃል፤”ወጣቱ አስተሳሰቡ ከገንዘብ ጋር ያልተያያዘ ቀና የሆነ ዜጋ ነው” በማለት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ሌሎች
ወጣቶችም የተማሩትን እንደ አቤል ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ አቶ ደረጄ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m