
አጼ ቴወድሮስ ከቋራ እስከ መቅደላ የሠሩትን ታሪክና አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከቋራ እስከ መቅደላ የማኅበረሰብ አቀፍ ኢኮ ቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክትን የተመለከተ የምክክር መድረክ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶክተር) ከዚህ ቀደም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ አንግበዋቸው የነበሩ የስልጣኔ ህልሞች በአግባቡ ለመገንዘብና የአሁኑ ትውልድ ከእርሳቸው ምን መማር እንደሚገባው ለማወቅ እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
በእንቅስቃሴውም በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ባሳተፈ መልኩ ሰፊ ሥራ መሠራቱን አውስተዋል። ከቋራ እስከ መቅደላ የማኅበረሰብ አቀፍ ኢኮ ቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክትን በተመለከተ ከመቅደላ 150ኛ ጉባዔ በኋላ የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን አውስተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሚዲያ ትውውቅ በሰፊው እንዲሠራ ከማድረግ ባሻገር የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን የመሠራትና ሀውልት የማቆም ሥራ መከናዎናቸውን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ግን አጼ ቴዎድሮስ በሠሩት ልክ ከቋራ እስከ መቅደላ የሠሩትን ታሪክና አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ በኩል ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አጼ ቴዎድሮስ አንድነቷ የተጠበቀና በስልጣኔ ማማ ከፍ ያለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያደረጉትን ጥረት ለማስቀጠልና የእርሳቸው አሻራ ያረፉባቸውን ቦታዎች የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተለያየ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ግርማ ታያቸው (ረዳት ፕሮፌሰር) ፕሮጀክቱ የአጼ ቴዎድሮስን እውነተኛ ታሪክ የማስተዋወቅ፣ ከ5ሺህ እስከ 8ሺህ ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ በኢኮ ቱሪዝሙ ላይ ማኀበረሰቡን አቀናጅቶ የመሥራትና አካባቢዎችን መልሶ የመገንባት ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።
አጼ ቴዎድሮስ ታሪክ የሠሩባቸውን ቦታዎች ለይቶ የማልማት፣ ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ ሎጂዎችን የመገንባት፣ መሰረተ ልማቶችን የማልማትና ወጣቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ተከታታይ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከንጋት ኢንተግሬትድ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ጋር በመተባበር በተዘጋጀው መርሃ ግብር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕግ አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ደራሲያን እንዲሁም አርቲስቶች ታድመውበታል።
ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ ካሣ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ