በትምህርት ዘመኑ በዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ችግር እንዳይኖር ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

344

ባሕር ዳር፡ መስከረም 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) የ2012 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርትን ለመጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቅቀው የተማሪዎችን መምጣት እየጠበቁ መሆኑን የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ፎረም አስታወቀ፡፡

የ2012 ዓ.ም የትምህርት መርሀ ግብርን ለማስጀመር የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ፎረም አስተባባሪ እና የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በተለይም ለአብመድ ገልፀዋል፡፡
በአማራ ክልል 10 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ፤ ተቋማቱ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ ፎረም ከመሰረቱ ቆይተዋል፡፡ ፎረሙ ካለፈው ዓመት ግንቦት ጀምሮ የ2012 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራን ሰላማዊ እና የተረጋጋ ለማድረግ አቅዶ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደነበር ነው አስተባባሪው የተናገሩት፡፡

የ2011 ዓ.ም አፈፃፀም ተገምግሞ እና ውስንነቶቹ ተለይተው ለ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የዕቅድ መነሻ በመሆን አገልግሏል ያሉት ዶክተር አባተ የመጀመሪያው የእቅድ ግምገማ ግንቦት እና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አፈፃፀም ደግሞ ነሐሴ ጨረሻ ላይ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ላይ እንደተገመገመ ነው ያስረዱት፡፡ ለግጭት መነሻ ምክንያት እየተደረጉ ያሉ የየተቋማቱ የመሠረተ ልማት እና የግብዓት አለመሟላት ችግሮችን በተቻለ መጠን ለመፍታት እንደተሰራም ተናግረዋል፡፡ ባለፈው የትምህርት ዓመት የችግሮቹ መጠን እና አይነት ይለያይ ይሆናል እንጂ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራን የሚያስተጓጉሉ ችግሮች ገጥመውን ነበር ያሉት ዶክተር አባተ የችግሮቹ ምንጮች ተለይተው በዚህ ዓመት እንዳይደገሙ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቅቋል ነው ያሉት፡፡

በላፈው ዓመት በአማራ ክልል በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠሩ ችግሮች ከኋላ ገፊ ምክንያቶች ቢኖሯቸውም መነሻቸው ግን የግብዓት እና የመሠረተ ልማት አለመሟላቶች ነበሩ ያለን የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት እና የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ኅብረት ፎረም አስተባባሪ ተማሪ ማተቤ ሙጨ ነው፡፡

ችግሮቹ እንዳይደገሙ ለማድረግ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉ የተማሪዎች ኅብረት አቅደው እየሰሩ መሆኑንም ነግሮናል፡፡ የየዩኒቨርሲቲዎቹ የተማሪዎች ኅብረት እቅድ ከቅበላ እስከ ግቢ ማላመድ እንደሚዘልቅም ነው የተናገረው፡፡ የተማሪዎች ኅብረት የተማሪዎች አቀባበል፣ ትውውቅ እና የየዩኒቨርሲቲዎቹን ህግና ደንብ ገለፃ ያካተተ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁም ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous article“ውል ሰጪም ተቀባይም እነማን እንደሆኑ አልታወቁም”፤ ትምህርት ቤቱም ከ14 ዓመታት በኋላም ሥራ አልተጀመረበትም፡፡
Next article“የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ካልለጠፍን ስምሪት አይሰጠንም፡፡” አሽከርካሪ