
“ሀብት ለማፍራት ብቻ ሳይሆን ያለውንም ለመጠበቅና ሕይወትን ለመታደግ የሠላም መኖር ወሳኝ ነው” ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጸጥታ መደፍረስ ክስረት በመሆኑ ሀብት ለማምጣት ብቻ ሳይሆን ያለውንም ለማስጠበቅና ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ሕይወት ለመታደግ የሠላም መኖር ወሳኝ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናግረዋል። በክልሉ 12 ተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ደስታ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ የጸጥታ እጦት የሀብት ክስረትን ከማስከተሉም በላይ ሕይወት ቀጣፊ ነው። ስለዚህ ተጨማሪ ሀብት ለማምጣት ብቻ ሳይሆን ያለውንም ለማስጠበቅና ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ሕይወት ለመታደግ የሠላም መኖር ወሳኝ ነው ብለዋል።
“ሠላም የማይኖር ከሆነ ብዙ ዓመታት ለፍተን የገነባናቸውን አንጡራ ሀብቶቻችንን ወድመው እንደገና የኋሊት ያስጉዘናል” ያሉት አቶ ደስታ፣ በእስካሁንም ሂደት የሰው ሕይወትን የቀጠፈና ሀብትን ያወደመ ነገር ቢኖር ዴሞክራሲ እጦት ያመጣው ሳንካ ነው ብለዋል።
“በዴሞክራሲ እጦት ምክንያት የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፤ ሀብት ንብረት ወድሟል፡፡ መንገድ መዝጋት፣ ድልድይና ንብረት ማውደም ያስፈለገው አንድን ነገር ለመቀየር ወይም መንግሥትን ከሥልጣኑ ለማስነሳት ሲባል ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ መንግሥትን ለመቀየር ግን በዚህ አካሄድ ሳይሆን ትንሽ ደቂቃ ተሰልፈን በካርዳችን መሆን አለበት ብለዋል።
በካርድ ከሆነ ውድመት፣ ጥፋትና መገዳደል ሳይኖር ባለው አማራጭ ፍላጎታችንን ማሳካት እንችላለን ያሉት ርዕሰመስተዳድሩ፣ በዚህም ዴሞክራሲን መለማመድ፤ ባሕሉን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል።
የዴሞክራሲ መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ምርጫው ሠላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ይኖርብናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በምርጫው ውጤትም አብዛኛው ሰው የተስማማበትን ማክበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ጊዜ በሲዳማ ክልል እየተካሄደ ያለው የምርጫ ዝግጅት እንቅስቃሴ ሠላማዊ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደስታ፣ በክልሉም 12 ተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን አቅርበው አስመዝግበዋል ብለዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሳንካ እንዳይገጥመው እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ሄደት ውስጥ ችግር ከገጠማቸው ወዲያው መፍትሄ ማግኘት እንዲችሉ የጋራ ምክር ቤት መስርተናል ብለዋል። የጋራ ምክር ቤቱ የገዢው ፓርቲ ሀሳብ በበላይነት የሚንጸባረቅበት ሳይሆን ሁሉም ድምጹ እኩል የሚያሰማበትና ችግሩ በእኩል ተፈትሾ በእኩል ደረጃ ፍትህ የሚያገኝበት መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ደስታ በሲዳማ ክልል ከሁለት ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ ተናግረዋል። ለእነዚህ ሁሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ተሰናድተዋል ብለዋል። የጸጥታ ጉዳዩን አስተማማኝ የማድረግ ሥራ በተለየ ትኩረትና ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ጭምር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም በመሆኑ እስካሁን በምርጫ ጉዳይ በክልሉ ያጋጠመ ችግር እንደሌለ ጠቁመዋል። ዘገባው የኢፕድ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ