በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችንና የተፈናቃዮችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሠሩ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥር የሚገኙ ሲቪል ማኅበራት አስታወቁ፡፡

77
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችንና የተፈናቃዮችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሠሩ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥር የሚገኙ ሲቪል ማኅበራት አስታወቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማኀበር ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ሥር ለሚገኙ ሲቪል ማኅበራት ተወካዮች በምርጫ ወቅት ያለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ ሥልጠና ሠጥተዋል።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ተወካይ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሰውሐረግ ጌታቸው አካል ጉዳተኞች በምርጫ ወቅት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና ፌዴሬሽን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ ሰውሐረግ ገለጻ አካል ጉዳተኞች ስለ ምርጫው በቂ መረጃ የማግኘት እድላቸው ከሌላው የጠበበ በመሆኑ ሲቪል ማኅበራት መረጃ ሊያደርሷቸው ይገባል፤ አካል ጉዳተኞች በምርጫ አይሳተፉም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመኖሩ ሲቪል ማኅበራት አካል ጉዳተኞች የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ማገዝ አለባቸው።
የማኅበረሰቡን 20 በመቶ የሚሸፍኑት እነዚህ የማኀበረሰብ ክፍሎች በምርጫ በማሳተፍ የሚያሥተዳድራቸውን ሊመርጡ ይገባል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ፖሊሲ ሲያዘጋጁ አካል ጉዳተኞችን ከግምት ማስገባት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሰውሐረግ አካል ጉዳተኞች የማኅበረሰቡ አንድ አካል በመሆናቸው በምርጫ ወቅት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች አካል ጉዳተኞች በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ አስበው መሥራት አለባቸውም ብለዋል። ተወካይ ፕሬዝዳንቷ አካል ጉዳተኞች ያገኙትን መረጃ ተጠቅመው መብታቸውን እንዲያስከብሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከድንበር የለሽ የበጎ አድራጎት ማኅበር ተሳተፊ አርቲስት ከፍያለው እሸቴ በተለይ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ተፈናቃዮች መብታቸውን ተጠቅመው የሚያስተዳድራቸውን እንዲመርጡ ለማስቻል እንደሚሠሩ ገልጿል፡፡ እንደ አርቲስት ከፍያለው ማብራሪያ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ተፈናቃዮች በምርጫ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተገቢ የሆኑ መረጃዎችን ማድረስ ይገባል። ተፈናቃዮች መብታቸው እንዳይጣስ በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ስምምነት የተፈረመ በመሆኑ በምርጫው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሲቪል ማኅበራት ኀላፊነታችን ሊወጡ ይገባል ብሏል።
ሲቪል ማኅበራት ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለተፈናቃዮች ተገቢውን መረጃ ማድረስ አለባቸው። አርቲስቱ ሲቪል ማኅበራት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው በምርጫ ወቅት በማኅበረሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ወከባና እንግልት ለማስቆም ሊሠሩ ይገባል ብሏል። በተሠጣቸው ሥልጠና መሰረትም ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ጉባኤ የባሕር ዳር አስተባባሪ አቶ ታድሎ ተስፋዬ ሲቪል ማኀበራት ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር በምርጫው ላይ የሚኖራቸውን ሚና ለማጉላት ሥልጠናው መዘጋጀቱንም ነው የነገሩን። የምርጫ ታዛቢ የሚሆኑ አባላትን የመመልመል ሥራውም ተጠናቋል ብለዋል።
“ምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚወዳደሩበት ሜዳ ነው” ያሉት አስተባባሪው በዚህ የፉክክር ሜዳ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕግን ብቻ መሰረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አስተባባሪው እንዳሉት በውድድሩ ወቅት ተወዳዳሪዎች የዜጎችን መብት ማክበር አለባቸው፤ ዜጎች የመምረጥ፣ የመመረጥ እና ድምጻቸው የመከበር መብት አላቸው፤ ሲቪል ማኅበራት እነዚህን መብቶቻቸውን የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው።
በኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የክትትል ባለሙያ አቶ ክንድዬ ብርሃን ምርጫ አንዱ የሠብዓዊ መብት ማረጋገጫ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ሲቪል ማኀበራት ምርጫን የመታዘብ ኃላፊነት ተሠጥቷቸዋል።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ እንዲሆን ሲቪል ማኅበራት መታዘብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ምርጫ ጣቢያውን በመከታተል ያለውን ሂደት ሪፖርት ያደርጋሉ። የሚታዩ ስህተቶች የሚስተካከሉበትን መንገድ በመጠቆም እንዲስተካከሉ ማድረግ እና የታዛቢነት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ሲቪል ማኅበራት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድሕረ ምርጫ ወቅት ንቁ ተሳታፊ በመሆን የመራጮች እና የተመራጮች መብት መከበሩን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ :- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሩሲያ የቀጣናውን ደኀንነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች፡፡
Next articleለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ቅድሚያ በመስጠት ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡