
አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች “ኢንቨስተር ነን” በሚል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል እንደሚፈፅሙ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ እንዳረጋገጠው አንዳንድ የውጭ
ሀገር ዜጎች “ኢንቨስተር ነን” በሚል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል በመፈፀም በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ገልጿል።
መረጃው እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሀብትና ንብረት
ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ማንነት በጥናት በመለየትና ቀረቤታ በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ወንጀል እየፈፀሙባቸው
መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል። እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የመጡ በማስመሰል፣ አብሯዋቸው
የሚሠሩ ኢትዮጵያዊያንን እንደሚፈልጉ በማግባባትና ለሥራ ማስኬጃም ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዳላቸው በመግለጽ
ኢትዮጵያዊያንን ካገኙ አብሮ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ በማስመሰል የሚያጭበረብሩ መሆናቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
ወንጀል ኢንተለጀንስ አሳውቋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን “አጭበርባሪዎቹ “ኢትዮጵያውያን አብረዋቸው ቢሠሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሳመን እና ከዚህ
በተጨማሪም ዶላር የማባዛት ችሎታ እንዳላቸው እንደሚገልጹም አመላክቷል፡፡
“አባዝቶ ለማሳየት መጀመሪያ የያዙትን ዶላር ሌላ ቦታ በፖስታ በመደበቅና ይባዛበታል ያሉትን ወረቀት ኬሚካል ውስጥ በመንከር
ከዚያም የተነከረውን ወረቀት አውጥተው እንዲደርቅ በማድረግ በሌላ ፖስታ ውስጥ ያስቀመጡትን ትክክለኛ ዶላር በእጥፍ
እንዳባዙት በማስመሰል ለሰዎቹ ያሳዩና ይበልጥ አመኔታን ለማግኘት ተባዛ ያሉትን ዶላር ባንክ ቤት ይዘው እንዲሄዱና
ትክክለኛነቱን አረጋግጠው እንዲመጡ ካደረጉ በኋላ አሁን የተባዛውን ዶላር ትክክለኛ መሆኑን ስላረጋገጥን እስከ አንድ ሚሊየን
ዶላር ይዛችሁ ኑና እናባዛ በማለት ወደ ማጭበርበር ተግባር እንደሚያስገቡ ታውቋል” ነው ያለው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፡፡
የኢትዮጵያን የብር ኖትም በእጥፍ ማባዛት እንደሚችሉ በማስረዳትና ሃብታም እንደሚሆኑ በማሳመን ዜጎች ያላቸውን ገንዘብ
ይዘውላቸው ሲሄዱ ግማሾቹ ከነገንዘቡ ታፍነው ገሚሶቹ ደግሞ ራሳቸውን ስተው እንደተገኙና ገንዘባቸውንም እንደተቀሙ
ማረጋገጥ ተችሏል ብሏል፡፡
የዚህ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባዎችም ቤተሰቦቻቸው መበተኑን፣ ለድህነትና ለጤና መታወክ መዳረጋቸውን ማረጋገጡን
የገለፀው ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ኅብረተሰቡ ሁኔታውን ተገንዝቦ “የማይገባ ጥቅም አገኛለሁ” ብሎ
ለእንደነዚህ አይነት “አጭበርባሪዎች” ሲሳይ እንዳይሆን እንዲሁም ራሱንና ቤተሰቡን መጠበቅ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥም በቅርብ ላሉ የጸጥታ አካላት ወይንም በነፃ የስልክ መስመር 987 በመደወል ጥቆማ መስጠት
እንደሚችል ማሳወቁን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m