
አልማ ግማሽ ሚሊየን ብር የሚገመት የቤት ክዳን ቆርቆሮ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአጣዬና አካባቢው ጉዳት ለደረሰባቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማህበር ድጋፉን ለሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና ለሰሜንሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስረክቧል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የአልማ ፋይናንስና ሎጅስቲክስ ዳይሬክተር ሰጥቷል ደሳለኝ እንደገለፁት፤ በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና አካባቢው በፀረ ሰላም ኃይሎች ቤታቸው ለተቃጠለባቸው፣ንብረታቸው ለተዘረፈባቸውና ለተፈናቀሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች አልማ ካለው በጀት ቀንሶ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
500 ሺህ የሚገመት የቤት ክዳን ቆርቆሮ አልማ ድጋፍ ሲያደርግ ድርጅቱ ከዜጎች ጎን መኾኑን ለማስታወስ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ማህበሩ እንደዚህ አይነት ድጋፎችን ከዚህ በፊት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፣በሁመራ አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ በኮሮና ቫይረስና በአንበጣ መንጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ሌሎችም ተቋማት የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ ዜጎችን መታደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንግዳሸት በጋሻው እንደገለፁት በዞኑ በአጣዬና አካባቢው በደረሰው ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በርካታ መሆናቸውን ገልፀው፤ እነዚህን መልሶ ለማቋቋም ኅብረተሰቡ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አልማ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች ከጎናቸው በመቆም ላደረገው ድጋፍ በዞኑ አስተዳደር ስም ምስጋና አቅርበዋል፤ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የዘገበው የኤፍራታና ግድም ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ