በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነቶች መረጃ አያያዝና አስተዳደርን ውጤታማ ያደርጋል የተባለ የመረጃ ቋት ማሻሻያ ወደ ሥራ ሊገባ እንደሆነ ተገለጸ።

239
በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነቶች መረጃ አያያዝና አስተዳደርን ውጤታማ ያደርጋል የተባለ የመረጃ ቋት ማሻሻያ ወደ ሥራ ሊገባ እንደሆነ ተገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ማሻሻያ የተደረገበት የመረጃ ቋት በ2014 በጀት ዓመት ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል። የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከሥነ ሕዝብ መረጃ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ላላቸው፣ የሕዝብ ብዛትንና ዕድገትን የሚወሰኑ እና ለኅብረተሰቡ ጥቅም ለሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ የዕቅድ ተግባራት ወሳኝ ነው።
ወሳኝ ኩነቶች ተብለው የሚጠሩት ደግሞ ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ እና ፍቺ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የእነዚህን ወሳኝ ኩነቶች መረጃ በሚገባ በማደራጀት ለሕግ፣ ለአስተዳደር ጉዳዮች እና ለስታትስቲክስ ተቋማት እንዲውሉ ወደ ሥራ አስገብቷል። በአማራ ክልልም ቢሮ በማደራጀት፣ የሰው ኀይል በመመደብ፣ የሥራ መሣሪያ በማሟላትና ገንዘብ በመመደብ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ምንም እንኳን በሚፈለገው ፍጥነት ሥራው እየሄደ ባይሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ የክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ባንቺአምላክ ገብረማርያም ተናግረዋል።
ኤጄንሲው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባንና የመረጃ አያያዝን ወደ ዘመናዊ የመረጃ ቋት ለማስገባት አቅዶ ተግባራዊ አድርጓል። ጥቅም ላይ የዋለው የመረጃ ቋት ግን መረጃን በሚፈለገው ደረጃ ይዘቶችን አካትቶ ለማደራጀት ክፍተት እንደነበረበት አስታውቀዋል። በዚህም ምክንያት ጥቅም ላይ የዋለውን የመረጃ ቋት የማሻሻል ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ማሻሻያው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ከማዘመን አልፎ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ አመላክተዋል። የሪፖርት አደረጃጀት ሥርዓቱ ጠንካራ እንዲሆን አዳዲስ የመረጃ ይዘቶች እንደተካተቱበትም ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
ቀጣይ የኦንላይን ምዝገባ ስርዓት በክልሉ እንዲኖር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ማሻሻያውን የሠራው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ባለሙያው ኪሩቤል አያልነህ እንዳለው ከዚህ ቀደም በክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሂደት መረጃን በጥራት ለማደራጀት የሚያጋጥም ክፍተት ነበር። እንደ ወጣት ኪሩቤል ማብራሪያ በምዝገባ ሂደቱ ተፈላጊ ይዘቶች ሳይሟሉ በቀሩ ጊዜ እንዲካተቱ ሊያደርግ የሚችል አሠራር አልነበረውም። አሠራሩም ወጥነት ይጎድለው እንደነበር አንስቷል።
የመረጃ ቋቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ተቋም ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ተፈላጊ መረጃዎችን በተመሳሳይ መልኩ ለማደራጀት አመቺ አልነበረም ብሏል። በዚህም ተቋማት የሚፈልጉትን መረጃ በቀላሉ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል። የተደረገው ማሻሻያም መረጃን በጥራት ወደ ቋቱ በማስገባት በየአስተዳደር እርከኑ ለሚመለከታቸው ተቋማት ተገቢውን ሪፖርት ለማድረስ ምቹ መሆኑን አብራርቷል።
በተቋማት የሚፈለጉ ተጨማሪ ይዘቶች እንዲካተቱ መደረጉንም አንስቷል። ማሻሻያው ቀላል እና ለመተግበር አመቺ መሆኑም ተጠቅሷል።
በተሻሻለው የመረጃ ቋት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ከሁሉም የአማራ ክልል ወረዳዎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ስልጠና በደብረ-ታቦር ከተማ እየተሰጠ ነው። ስልጠናውን ተከትሎ የማሻሻያውን መሠረታዊ ዓላማ በመረዳት ሰልጣኞች ውጤታማ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እንዲያከናውኑ ይጠበቃል። ሰልጣኞችም ከዚህ ቀደም የነበረው የአሠራር ችግር እንደሚቀረፍ ተስፋ አድርገዋል። በሚሠጣቸው ስልጠና መሰረት ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፣ የመረጃ ቋቱ ከዚህ በፊት ይሰሩበት ስለነበር ማሻሻያውን በቀላሉ ለመላመድ እንደማይቸገሩም አንስተዋል።
ማሻሻያ የተደረገበት የመረጃ ቋት በ2014 በጀት ዓመት ጥቅምት ላይ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል። ለዚህም ባለሙያዎች በቀጣይ የተግባር ልምምድ እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ- ከደብረ-ታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሕዝበ ሙስሊሙ ታላቁ የረመዳን ወር እስላማዊ አስተምሕሮን በመከተል በመረዳዳትና በመተጋገዝ ማሳለፍ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ።
Next articleአልማ ግማሽ ሚሊየን ብር የሚገመት የቤት ክዳን ቆርቆሮ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአጣዬና አካባቢው ጉዳት ለደረሰባቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ፡፡