ሕዝበ ሙስሊሙ ታላቁ የረመዳን ወር እስላማዊ አስተምሕሮን በመከተል በመረዳዳትና በመተጋገዝ ማሳለፍ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ።

332
ሕዝበ ሙስሊሙ ታላቁ የረመዳን ወር እስላማዊ አስተምሕሮን በመከተል በመረዳዳትና በመተጋገዝ ማሳለፍ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ።
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ ሙሃመድ 1 ሺህ 442ኛው ሂጅራ የረመዳን ወርን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ታላቁ የረመዳን ወር እስላማዊ አስተምሕሮን በመከተል በመረዳዳትና በመተጋገዝ ማሳለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
እስልምና ሃይማኖት ከተገነባባቸው አምስት መሰረቶች አንዱ የረመዳን ጾም ነው፤ይህን የጾም ወር ካላስፈላጊ ተግባሮች በመራቅ መጾም ከአላህ ግዴታ ተደርጓል ብለዋል ሼህ ሰኢድ፡፡ በቁርዓን ሕግ የረመዳንን ወር ከአላህ ምህረት በመፈለግ እንደሚጾምም ገልጸዋል፡፡
ታላቁን ረመዳን ወር በጾም ከማሳለፍ በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ለተቸገሩ ወገኖች በማብላት፣ በማጠጣት፣ በመደጋገፍ እና በመተጋገዝ ጭምር መሆን እንደሚገባውም መክረዋል፡፡
ረመዳን ቁራዓን የወረደበት ታላቅ ወር በመሆኑ ማንኛውም አማኝ ቁራዓንን መቅራት አለበት ብለዋል፡፡
ጾሙ ከፈጣሪ ተቀባይነት እንዲኖረው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በእስላማዊ አስተምሕሮና “ዘካን” በማብዛት፤ ሌሊቱን ደግሞ “ሶላት” በመስገድ ማሳለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አማኙ ከሚያገኘው ገቢም ለምስኪኖች እና ለድሃዎች ማገዝ እንደሚገባውም መክረዋል፡፡
በዚህ ወቅት በኢትዮጵያና በዓለም የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሊያደርስ የሚችለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ቀውስ “አላህ” እንዲያከስመው “ዱዓ” ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ትምሕርት እና በመንግሥት የሚወጡ ሕጎችን በማክበር የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ሀገራዊ ጥረትም ኅብረተሰቡ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሀገሪቱ የሚስተዋለው የዜጎች ሕይወት መጥፋት እና መፈናቀል እንዲቆም በ“ዱዓ” ፈጣሪን መለመን ይገባልም ብለዋል፡፡ ዜጎች በፍቅር፣ በሰላምና በጋራ እንዲኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኀላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ለመወጣት እየሠሩ መሆናቸውን አሚኮ ያነጋገራቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትች አስታወቁ፡፡
Next articleበአማራ ክልል የወሳኝ ኩነቶች መረጃ አያያዝና አስተዳደርን ውጤታማ ያደርጋል የተባለ የመረጃ ቋት ማሻሻያ ወደ ሥራ ሊገባ እንደሆነ ተገለጸ።