
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማግኘት እንደሚገባ ኢትዮጵያ ታምናለች” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቅርቡ የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡት ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በመመረጣቸው አቶ ደመቀ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በሚኖራቸው የሥራ እንቅስቃሴ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠውላቸዋል።
አቶ ደመቀ በቅርቡ በኪንሻሳ የተካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ ለምክትል ሊቀመንበሯ አብራርተዋል፡፡ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸው በማመን በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል በኢትዮጵያ በኩል ጽኑ እምነት ያለ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።
በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በመሻሻል ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” መርህ በአፍሪካ ሕብረት በኩል በጽኑ የሚታመን መርህ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በዚህ አንጻር ለያዘችው አቋም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕብረቱ ሠራተኞች ክትባት አንዲደርሳቸው በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበዋል።
አቶ ደመቀ ለአፍሪካ ሕብረት ሠራተኞች ተገቢው የክትባት አገልግሎት እንዲደርሳቸው ማደረጉ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ ለተፈጻሚነቱም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሠራ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
