ምርጫው በአግባቡ እንዲካሄድ የጸጥታ አካላት ከአሁኑ ነጻና ገለልተኛ ኾነው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የከፍተኛ ትምሕርት ተቋም መምህራን ገለጹ፡፡

116
ምርጫው በአግባቡ እንዲካሄድ የጸጥታ አካላት ከአሁኑ ነጻና ገለልተኛ ኾነው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የከፍተኛ ትምሕርት ተቋም መምህራን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በመሠረታዊ መርኾዎች ላይ የተመሰረተና ነፃ፣ ተዓማኒ እና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው። ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ያዳብራል፤ ሕዝባዊ አንድነትን የማጎልበትና አብሮ የመኖር ዕሴት የመገንባት ፋይዳ እንዳለውም በመርህ ደረጃ ይታመናል፡፡
ስድስተኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እንቅስቃሴ የተጀመረው በኢትዮጵያ ተደራራቢ ችግሮች ባሉበት ወቅት ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸም ይስተዋላል፤ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሠላምና የልማት ጥናት ትምሕርት ቤት መምህሩ አልዩ ውዱ (ዶክተር) እንዳሉት የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ ውጥረት እና ጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻዎች በሀገሪቱ ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ናቸው፡፡ ምርጫውን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችል የጸጥታ ስጋትም አለ ይላሉ መምሕሩ፡፡ ችግሮቹ ተዳምረው ለቁጥጥር የሚያዳግት የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም ነው ዶክተር አልዩ ያስታወቁት፡፡
ዶክተር አልዩ በምርጫ ሂደቱ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይገባል፤ በተለይ በድሕረ ምርጫ ሁሉም አካል አብላጫ የሕዝብ ድምጽ ያገኘን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሕዝብ በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ያስተዳድረኛል የሚለውን በነጻነት እንዲመርጥ፣ ኮሮጆ እንዳይገለበጥ፣ የምርጫ ውጤት እንዳይጭበረበር እና ማንም ባልተገባ መንገድ ስልጣን ለመቆናጠጥ እንዳይጥር ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
ለዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ እና የምርጫ ጣቢያ ታዛቢዎች እንዲሁም የጸጥታ አካላት በከፍተኛ ኀላፊነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል፡፡ መራጮችም የሰከነ አካሄድን መከተል አለባቸው ብለዋል፡፡
በተለይ የጸጥታ አካላት ምርጫው በአግባቡ እንዲካሄድ ከአሁኑ ነጻና ገለልተኛ ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ ያልተገባ አካሄድ የሚከተሉ የፖለቲካ ተዋናዮች ከተፈጠሩ መገሰጽ ይገባልም ብለዋል፡፡ ለዚህም አላስፈላጊ አዝማሚያ ያላቸው የጸጥታ አካላት ካሉ ከአሁኑ መታረም እንዳለባቸው ነው ያነሱት፡፡
ያለፉት ምርጫዎች ሂደት የይስሙላ፣ የፖለቲካ ምሕዳራቸው የጠበበ፣ ሕዝብ ያላመነባቸው እና ግጭቶች የታዩባቸው እንደነበሩ የገለጹት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምሕሩ ጀማል ሰይድ ናቸው፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዓላማውን እንዲያሳካም ካለፉት ምርጫዎች ትምህርት መውሰድ፣ ከሌሎች ሀገራትም ልምድ መቅሰም እና በጥንቃቄ ማካሄድ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ በቅድመ ምርጫው ከሞላ ጎደል አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ቢሆንም በየጊዜው የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የጸጥታ መዋቅሩ ከፓርቲዎች ተጽዕኖ ነጻ ኾኖ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በዋናነት በድህረ ምርጫ ሊፈጠሩ የሚችሉ ቀውሶችን ለማስቀረትና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር መምሕሩ ሙሉጌታ ሐሰንም የምርጫ ውጤትን በጸጋ አለመቀበል በአፍሪካ እየተለመደ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የሕዝብ ድምጽ ያለ አግባብ እንዳይዘረፍ መሪው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤትን በአግባቡ መቀበል እንደሚገባቸው የመከሩት መምህሩ ቀደም ብሎ ግን ሰላማዊ ምርጫ ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም በተለይ የጸጥታ አካላት በየቦታው የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ውጤታማ በሆነ መልኩ መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያስታወቁት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ ለስኬታማነቱ መሥራት ይገባል” የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ
Next articleስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ሊኖር እንደሚገባ አሚኮ ያነጋገራቸው እናቶች ተናገሩ፡፡