
የኮሮናቫይረስ ክትባት አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሃይማኖት አባቶች ኅብረተሰቡ አሁን ላይ እየተሠጠ ባለው የክትባት አገልግሎት ሳይዘናጋ የኮሮናቫይረስ መከላከያ መንገዶችን አጠናክሮ መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ኅብረተሰብም በአንዳንድ አካላት በሚነሱ የሀሰት መረጃዎች ምክንያት ሳይዘናጋ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ የመከላከያ እርምጃዎችን በተሟላ መልኩ መተግበር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ አሁን ላይ እየተሰጠ ያለው የኮሮናቫይረስ የክትባት አገልግሎትም በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የብጹዕ ወቅዱስ ፖትሪያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤትና የውጪ ጉዳይ መምሪያ የበላይ ኀላፊ ብጹዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ቡጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዉያን፣ በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስትያን የኢትዮጵያ ዩኒየን ፕሬዝዳንት ፓስተር ታደሰ አዱኛ የኮሮናቫይረስ ክትባት ወስደዋል፡፡
አሁን ላይ በሀገሪቱ እየተሰጠ ባለው የኮሮናቫይረስ ክትባት ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የጤና ባለሙያዎች ተከትበዋል፤ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ከ55-64 ዓመት ሆነው የሚታወቅ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ክትባት እየተሰጠ እንደሚገኝ ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
በኮሮናቫይረስ የሚያዙ፣ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ ሕብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ