ለቅድመ መደበኛ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

1740
ለቅድመ መደበኛ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ቅድመ መደበኛ ትምህርት ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሥርዓት ቀድሞ የሚሰጥ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት እንዳለበት አሚኮ ያነጋገራቸው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ምሁር አስናቀው ታገለ (ዶክተር) አመላክተዋል፡፡
የስነ ልቦና ምሁሩ እንዳብራሩት እድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት ዓመት የሆናቸው ሕጻናት የሚውሉበት ትምህርት ቤት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ይባላል፡፡ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ልጆች ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲውሉ ለማድረግና የእናቶችን የሥራ ጫና ለመቀነስ የተጀመረ የትምህርት ሥርዓት ነው፤ ቅድመ መደበኛ ትምህርት በሀገሪቱ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል ባይባልም በርካታ ሕጻናት በሂደቱ እንዲያልፉ ተደርገዋል፤ ሕጻናት በቅድመ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥርዓት መማራቸው በቀላሉ ከሰዎች ጋር እንዲግባቡ፣ ንጽህናቸው እንዲጠብቁ፣ በራሳቸው መመገብ እንዲችሉ በማደረግ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
ዶክተር አስናቀው ሕጻናት በዚህ እድሜያቸው “መማር ይችላሉ” ወደሚለው ማደማደሚያ መደረሱን እና ትምህርት እንደ መደበኛ እየተሰጣቸው መሆኑን አይስማሙበትም፡፡ “ይህ አካሄድ ስህተት ነው” ብለዋል ዶክተሩ፡፡ ምክንያቱም ሕጻናት በዚህ እድሜያቸው የአማርኛና የእንግሊዘኛ ፊደል፣ ቁጥር እና ሌሎችንም ነገሮች እንዲማሩ መደረጉ በቀጣዩ የሕይወት ምዕራፋቸው ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ “ሕጻናት በቅድመ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥርዓት ላይ መሳተፋቸው በመደበኛው የመማር ማስተማር ሥርዓት ውጤታማ ያደርጋቸዋል” የሚሉ ጥናቶች መኖራቸውን ምሁሩ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጅ በቅደመ መደበኛ ትምህርት ላይ የተሳተፉ ሕጻናት ወደ መደበኛው የመማር ማስተማር ሥርዓት ሲቀላቀሉ በጥበብ ካልተያዙ በስተቀር ስልቹ እንደሚሆኑ እና ትምህርት ቤትን እንደ ግዳጅ እንደሚቆጥሩት በርካታ አጥኚዎች መስማማታቸውንም ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
ምሁሩ እንዳሉት በጥናት ላይ ተመስርተው እየሠሩ ያሉ ሀገራት ሕጻናት በተሻለ ቦታ እንዲውሉና አካባቢያቸውን በቀላሉ እንዲረዱ በማድረጋቸው ውጤት አምጥተዋል፡፡ ሕጻናት በቅድመ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ሲሳተፉ ፊደል እንዲቆጥሩ ሳይሆን እየተዝናኑ እና እየተጫወቱ አካባቢያቸውን እንዲረዱ መደረግ አለበት፡፡ በግልም ሆነ በመንግሥት እየተሰጠ ያለው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ወጥነት የሌለውና የመደበኛውን ትምህርት ሥርዓት የተከተለ በመሆኑ የተሻለና ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ መቅረብ አለበት፡፡ ምሁሩ ለአብነት እንዳነሱት አንዳንድ ያደጉ ሀገራት ሕጻናት በአምስት ዓመታቸው ቅድመ መደበኛ ትምህርትን እንዲጀምሩ ያደርጋሉ፤ በሁለት ዓመታትም እንዲጠናቀቅ ይደረጋል፤ ይህም ሕጻናቱ ሳይሰለቹ ወደ መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት ስለሚቀላቀሉ ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡
የኢትዮጵያን እና የሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ቅድመ መደበኛ ትምህርት ሥርዓት ያነሱት ዶክተር አስናቀው ሕጻናቱ ከአራት ዓመት ጀምሮ ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንደሚቀላቀሉ ጠቅሰዋል፡፡ ከሦስት ዓመት ተኩል ጀምሮ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሕጻናት መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ዘርፉ ውጤታማ መሆን ተስኖታል ባይ ናቸው፡፡
እንደ አማራ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ በመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ሕጻናትን ለማዋል ብቻ ተብሎ እየተሠራ ያለው ሥራ ሊቆም እንደሚገባ ዶክተሩ ጠቁመዋል፡፡ በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ከፍተኛ ልዩነትን ያስተናገደ በመሆኑ የተቀራረበ ነገር እንዲመጣ በትኩረት እንዲሠራም የስነ ልቦና መምህሩ መክረዋል፡፡
ምሁሩ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን በዘርፉ ያልሰለጠኑና ሕጻናትን ይዞ ለመዋል ብቻ ተብለው የተመደቡ ስለ መሆናቸው ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ አንዳንድ የቅድመ መደበኛ መምህራን ደግሞ በዘርፉ ያልሠለጠኑ በመሆናቸው ተማሪዎች ከእድሜአቸው በላይ እንዲማሩ እየተገደዱ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች የሚያስከትሉትን ተፅዕኖ ለመቅረፍ ዶክተር አስናቀው በመፍትሔነት እንዳነሱት መንግሥት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ለመስጠት ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ አለበት፤ መምህራንን በዘርፉ ማሰልጠን፣ የመማሪያ አካባቢን ምቹ እና የሕጻናቱን እድሜ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት አስተባባሪ አቶ ታማኝ አሸናፊ በዘርፉ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረውዋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የቅድመ መደበኛ ሥርዓተ ትምህርት ነባር እና አሁን ያለውን የቅድመ መደበኛ ትምህርት የማይመጥን እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡ እነዚህ እና መሰል ችግሮች ዘርፉ በጥራትም በሽፋንም አመርቂ የሚባል ውጤት አለማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡
አስተባባሪው እንዳሉት ችግሩን በመረዳት ቅድመ መደበኛ ይባል የነበረው የትምህርት ሥርዓት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ተብሎ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት እየተዘጋጀ ነው፤ የሚዘጋጀው ሥርዓት ትምህርት በሁለት ዓመታት የሚጠናቀቅ ሆኖ ደረጃ አንድ እና ደረጃ ሁለት ተብሎ ይከፈላል፡፡ ትምህርቱን በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በተሟላ ሁኔታ ለመስጠት ታቅዷል፡፡ በሰለጠነ የሰው ኀይል እንዲሰጥም በክልሉ ባሉ በአስሩም የትምህርት ኮሌጆች መምህራንን ለማሰልጠን እቅድ ተይዟል፡፡
አቶ ታማኝ እንደገለጹት በ2013 ዓ.ም በቅድመ መደበኛ የትምህርት ሥርዓት
• 752 ሺህ 847 ተማሪዎች በመንግሥት
• 77 ሺህ 343 ተማሪዎች ደግሞ በግል ትምህርት ቤቶች ለማስተማር እቅድ ተይዞ ነበር፡፡
እስካሁንም
• 600 ሺህ 237 ተማሪዎች በመንግሥት ትምህርት ቤት
• 18 ሺህ 278 ተማሪዎች በግል ትምህርት ቤቶች ገብተው እየተማሩ ነው፡፡ አፈጻጸሙም በድምሩ 74 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleቤትኪንግ ኢትዮጵያ ዛሬ በድሬድዋ ከተማ ይጀመራል፡፡
Next articleበኖርዲክ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃግብር በመጪው ቅዳሜ ይካሄዳል፡፡