ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ዛሬ በድሬድዋ ከተማ ይጀመራል፡፡

387
ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ዛሬ በድሬድዋ ከተማ ይጀመራል፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሮናቫይረስ መከላከያ ፕሮቶኮልን ተከትሎ በአዲስ መልክ በተወሰኑ ስታዲየሞች እየተስተናገደ ያለው እና ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የቀጥታ ስርጭት ዕድል ያገኘው የ2013 ዓ.ም ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ቀጣይ መርኃግብር ዛሬ በድሬዳዋ ስታዲየም ይጀመራል፡፡
13 ክለቦች እየተሳተፉበት የሚገኘው ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ታኅሣሥ 3 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ተጀምሮ ከጅማ እስከ ባሕር ዳር መርኃግብሮቹን አጠናቆ ወደ ድሬዳዋ በማቅናት ዛሬ ውድድሩን 10 ስዓት ላይ ይጀምራል፡፡
በባሕር ዳር የነበረው መርኃግብር ስኬታማ እና ሰላማዊ ሆኖ የተጠናቀቀ ነበር ያሉት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለዝግጅቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለነበራቸው የባሕር ዳር ከነማ ቦርድ አመራር እና ለከተማ አስተዳደሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የባሕር ዳር ስታዲየም ምቹ መሆን፣ በከተማዋ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች በበቂ ሁኔታ መኖር እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተባባሪነት ለውድድሩ ስኬት ምክንያቶች ነበሩ ተብሏል፡፡
ሦስተኛው የክልል ከተሞች ውድድር ዛሬ 10 ስዓት ላይ በሚካሄድ ውድድር በድሬዳዋ ይጀመራል ያሉት አቶ ክፍሌ እስከ ሚያዚያ 20/2013 ዓ.ም በሚኖረው የድሬዳዋ ቆይታም 30 ጨዋታዎች ይስተናገዳሉ ብለዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ መከላከያ ፕሮቶኮልን የተከተለው መርኃግብር ውድድሮቹ ከሰዓት በፊት 3 ስዓት እና ከስዓት በኋላ ደግሞ 10 ስዓት ቢሆንም በድሬድዋ ያለው አየር ንብረት ከበድ ያለ በመሆኑ ምሽት ላይ እንዲካሄድ ተወስኗል ተብሏል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የድሬዳዋ እግርኳስ ክለብ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የስታዲየሙን መብራት እንዲሠራ ተደርጓል ያሉት አቶ ክፍሌ ውድድሩን ከሚያሰራጨው ብዙኃን መገናኛ ጋርም ሰፊ ውይይቶች እና ድርድሮች ተደርገዋል ተብሏል፡፡
እንደ አቶ ከፍሌ ገለጻ ከሆነ የድሬዳዋ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ መርኃግብሩ ሐዋሳ ላይ በሚካሄድ ውድድር ፍጻሜውን ያገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአማራ ክልል ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰራጨውን የተዘዋዋሪ ብድር የመለሱ ወረዳዎች 41 ብቻ መሆናቸውን የአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
Next articleለቅድመ መደበኛ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡