በአማራ ክልል ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰራጨውን የተዘዋዋሪ ብድር የመለሱ ወረዳዎች 41 ብቻ መሆናቸውን የአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

540
በአማራ ክልል ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰራጨውን የተዘዋዋሪ ብድር የመለሱ ወረዳዎች 41 ብቻ መሆናቸውን የአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሥራ እድል ለመፍጠር የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እና የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮን መረጃን መሰረት በማድረግ የአስር ዓመት ዕቅድ መታቀዱን የአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ባንችይርጋ መለሰ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት አጠቃላይ ከክልሉ ሕዝብ 19 በመቶው ሥራ ፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ አምስት ዓመታትም የሥራ ፈላጊዎችን ቁጥር ወደ 12 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ኃላፊዋ ገልጸውልናል፡፡
በ2013 ዓ.ም ሥራ ለመፍጠር ከታቀደው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎች በዘጠኝ ወሩ ማሳካት የተቻለው 62 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 80 በመቶው ቋሚ እንዲሆን የሚጠበቅ ቢሆንም 57 በመቶ ብቻ ነው በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለው፡፡ የተቋማት የቅንጅታዊ አሠራር ችግር፣ በቂ የሆነ ድጋፍ እና ክትትል አለማድረግ ለእቅዱ አለመሳካት በምክንያትነት ተቀምጠዋል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራው ቋሚ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል ችግሮች መኖራቸውን ኅላፊዋ አንስተዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር እና የኮሮናቫይረስ ስርጭት በአገልግሎት እና በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በተሠማሩ ኢንተርፕራይዞች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አንስተዋል፡፡
የተዘዋዋሪ ብድር አመላለስ ችግር በመኖሩ ለወጣቶች መልሶ ለማሰራጨት አለመቻሉንም ኅላፊዋ አንስተዋል፡፡ በዚህም በክልሉ ካሉ ወረዳዎች 41 ብቻ ናቸው 97 በመቶ ብድር በማስመለስ መልሰው ለወጣቶች ማሰራጨት የቻሉት፡፡
በብድር አመላለስ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተዘዋዋሪ ብድር ተሰራጭቷል፡፡
የክልሉ መንግሥት የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በሀገርአቀፍ ደረጃ ከተሰራጨው በተጨማሪ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መመደቡን ኅላፊዋ ገልጸዋል፡፡ በገጠር በእንስሳት እርባታ፣ በወተት እና ወተት ተዋጽኦ፣ በንብ ማነብ እና ማርን በማቀነባበር እና በሰብል ምርት የሥራ ዘርፎች ወጣቶች እንዲሠማሩ መደረጉንም ነግረውናል፡፡
በቢሮው የትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ኅላፊ አቶ ድረሴ እሸቱ ከሚያዝያ 2/2013 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 6/2013 ዓ.ም በደሴ ከተማ አስተዳደር የክህሎት፣ የጥናት እና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጅ ውድድርና ሲምፖዚየም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበት የንግድ ትርዒት እንደሚካሄድም ነው የገለጹት፡፡ የደረጃ ሽግግር ያደረጉ ኢንተርፕራይዞች የዕውቅና ፕሮግራም እንደሚካሄድም አንስተዋል፡፡ ይህም ኢንተርፕራይዞች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጀው ፕሮግራም በመሳተፍ የውጭ ምርትን ቴክኖሎጅዎችን ተክቶ ለመሥራት ያስችላል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት በኩል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት አላት” ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ
Next articleቤትኪንግ ኢትዮጵያ ዛሬ በድሬድዋ ከተማ ይጀመራል፡፡