
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እየተገነባ ያለው የዓባይ ድልድይ ግንባታ በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የድልድዩ ምክትል ተጠሪ መሀንዲስ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከ60 ዓመታት በፊት በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባው ነባሩ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ለበርካታ ዓመታት የሕዝቦችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊና የፖለቲካዊ መስተጋብር እንዲጎለብት አድርጓል።
ሀገሪቱ ከጊዜ ወደጊዜ የምጣኔ ሀብቷ እያደገ፣ የሕዝብ ብዛቷና የተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የድልድዩ አገልግሎት የመስጠት አቅም ተዳክሟል። እድሜ ጠገቡን ድልድይ በየወቅቱ እየጠገኑም ቢሆን መጠቀም የግድ ሆኗል። ድልድዩ ጠባብና ላለው ወቅታዊ አገልግሎት የማይመጥን በመሆኑ ተሽከርካሪዎች መስመሩን ዘግተው በየወረፋቸው ለመተላለፍ ተገድደዋል። ይህ ደግሞ መንገደኞችም ሆነ አሽከርካሪዎች በወቅቱ ወዳሰቡበት እንዳይደርሱ ጫናን እያሳደረ ይገኛል።
አቶ ሣሙኤል ደምሴ የሚኖሩት በባሕር ዳር ከተማ ነው፣ የሚተዳደሩትም በታክሲ አገልግሎት መስጠት ሥራ ነው። አገልግሎት እየሰጠ ያለው ነባሩ የዓባይ ወንዝ ድልድይ በተለይ ጠዋትና ማታ ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍሰት ያለው በመሆኑ በወረፋ እየተስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ያለውን ችግር ለመፍታት ታዲያ ለአካባቢዉ ሁለንተናዊ እድገት ተስፋ የተጣለበት አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ እየተገነባ ይገኛል፡፡
1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት ወጪ የተመደበለት ድልድዩ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የካበተና ብዙ ተሞክሮ ባለው የቻይና ኮሙኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) ተቋራጭ እየተገነባ ነው፡፡ የግንባታውን የቁጥጥርና የማማከር ሥራ የሚያካሂዱት “ቦቴክ ቦስፈረስ’’ የተባለ የቱርክ አማካሪ ድርጅት ከስታዲያ የምህንድስና ሥራዎች ተቆጣጣሪ ድርጅት ከተባለ ሀገር በቀል አማካሪ ድርጀት ጋር በጋራ በመሆን ነው:: ድልድዩን በባለቤትነት የሚያስገነባው ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሲሆን ሙሉ ወጪው የሚሸፍነው በፌዴራል መንግሥት ነው፡፡
ዓባይ ወንዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ800 በላይ ኪሎሜትር ይጓዛል፡፡ በጉዞውም ስምንት ድልድዮችን እንደሚያቋርጥና አሁን በግንባታ ላይ የሚገኘው አዲሱ ድልድይ ዘጠነኛ መሆኑን በስታዲያ የምህንድስና ሥራዎች ተቆጣጣሪ ድርጅት የድልድዩ ምክትል ተጠሪ መሀንዲስ ፍቅረሥላሴ ወርቁ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡
የድልድዩ ግንባታ አሁን ላይ 43 በመቶ መድረስ የነበረበት ቢሆንም 27 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በግንባታው ሂደት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት እና ዓባይ ወንዝ በክረምት እየሞላ በማስቸገሩ ሥራው በታቀደው ልክ እንዳልተከናወነ ኢንጂነሩ ጠቁመዋል፡፡
ግንባታው በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋራጩ የሰው ኃይልና የግንባታ ማሽኖችን ቁጥር በመጨመር እንዲሁም ማታም ቀንም በመሥራት የዘገየበትን ጊዜ ለማካካስ እየሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የዓባይ ወንዝ ድልድይ በአይነቱ፣ በጥራቱና በዘመናዊነቱ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የሆነ፤ የገመድ ላይ ተወጣሪ የድልድይ ዓይነት እንደሆነ፣ ድልድዩ ሁለት ተሸካሚ ማማዎችን እና በማማዎቹ መካከል ሦስት ክፍሎች እንዳሉትም አስረድተዋል፡፡
ኢንጂነር ፍቅረሥላሴ እንደነገሩን ድልድዩ 380 ሜትር ይረዝማል፣ የጎን ስፋቱ ደግሞ 49 ሜትር ሲሆን በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ 6 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ባለሁለት አቅጣጫ የብስክሌት ተጠቃሚዎች መስመር እና 5 ሜትር የእግረኛ መሄጃን ያካተተ እንደሆነም ኢንጂነሩ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ድልድይ በነባሩ ድልድይ ላይ የሚታየውን የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ከመቀነስ ባለፈ ለከተማዋ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ ግንባታው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የድልድዩ ዲዛይን ለ100 ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ የተደረገ በመሆኑ ጥራት ያላቸዉንና ደረጃቸው ከፍ ያሉ የግንባታ ቁሳቁስ በሥራ ላይ እየዋሉ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
ድልድዩ 6 ሺህ ቶን ክብደት የመሸከም አቅም እንዳለው ያስረዱት ኢንጂነር ፍቅረሥላሴ በአጠቃላይ ለ400 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ