
የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ፋብሪካዎቹ ወደ ትግበራ እየገቡ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በ2008 ዓ.ም የተቋቋመው እና በሁለት ምዕራፍ እየተገነባ የሚገኘው የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ፋብሪካዎቹን ወደ ምርት ማስገባት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ ፕሮጀክቶቹን በሁለት ምዕራፍ በመክፈል ስምንት ፋብሪካዎችን በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እየገነባ ይገኛል፡፡ የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳንኤል ጌራ (ኢንጂነር) እንዳሉት በመጀመሪያው ምዕራፍ ተግባራዊ እየሆኑ የሚገኙት አራት ፋብሪካዎች ወደ ማምረት መግባት ጀምረዋል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ ከተገነቡት የኤሌክትሪክ ኃይል ትራንስፎርመር ማምረቻ እና መጠገኛ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩን ኢንጂነር ዳንኤል ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎቹ ሦሰት ፋብሪካዎች ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ፋብሪካዎች የተካተቱበት የሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት ማሽኖችን ለማስገባት ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ኢንጂነር ዳንኤል ነግረውናል፡፡
የክልሉ መንግሥት ሀሳቡን ከማንጨት ጀምሮ ለኢንተርፕራይዙ እውን መሆን ያላሰለሰ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ኢንጂነር ዳንኤል የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ለችግር መፍትሔ በመሆንና ቴክኖሎጂን በማሸጋገር በኩል ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የነበረውን ክፍተት የሚሞላ እንደሆነም ነው የጠቀሱት፡፡
የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ አሁን ላይ ከዲዛይን ጀምሮ ተወዳዳሪ እና ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራቱንም አስታውቀዋል፡፡ የራሱ ባለሙያዎችን በመጠቀም ከውጭ ሀገር ይገቡ የነበሩ ማሽኖችን በመተካትም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ኢንጂነር ዳንኤል ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም በውጭ ሀገር ዜጎች ሲሠራ የነበረውን የኢንዱስትሪ ሸዶችን በራስ አቅም ማምረትን በማዳበር የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሸድን መሥራት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡ ኢንጂነር ዳንኤል የማሽን ቴክኖሎጂው የውጭ ምንዛሬን ወጪን በማስቀረትም የራሱን አስተዋፅዖ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በወቅቱ በሀገር ውስጥ ካሉ የማሽን ቴክኖሎጂዎች የተሻለ የሚባል እንደሆነም ነው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው የጠቀሱት፡፡
ኢንተርፕራይዙ ፋብሪካ ግንባታዎችን በማከናወን ባለሀብቶች በማሽን እጦት የሚያባክኑትን ጊዜ እና ገንዘብ በሚቆጥብ ሁኔታ በአጭር ጊዜ መፍትሔ መስጠት እንደሚችል ኢንጂነር ዳንኤል አስታውቀዋል፡፡ ከሚፈጥረው የሥራ እድል በተጨማሪ በዘርፉ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ እንደሆነ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር ዳንኤል መረጃ ባሕር ዳር ላይ ያለው የማሽነሪ ማምረቻ ፋብሪካ በዓመት በሦስት ፈረቃ 36 ሺህ ማሽነሪዎችን ማምረት አቅም አለው፡፡ ኮምቦልቻ ላይ የሚገኘው ደግሞ በአንድ በዓመት 54 ሺህ ማሽነሪዎችን ማምረት ይችላል፡፡
ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የልማት አቅም ከፍ እንደሚያደርጉ ነው ኢንጂነር ዳንኤል ያስታወቁት፡፡ በአነስተኛ፣ በመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ እና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች የተሠማሩ ባለሀብቶች የሚፈልጉትን ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ