“የዓባይ ወንዝ የዘገየ ፍትሕ”

277
“የዓባይ ወንዝ የዘገየ ፍትሕ”
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት 10 ዓመታት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በጉልህ ይነሳል- በዓባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል ያለው ውዝግብ፡፡
አንዳንድ የዜና ማዕከላት ደግሞ ጉዳዩን “የውኃ ጦርነት” አድርገው ሲዘግቡትም ይስተዋላል፡፡
በየወቅቱ የሚወጡት የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ውዝግብ ዘገባዎች ከታሪካዊ ዳራ፣ ከዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም እና ስምምነት እንዲሁም ከቴክኒካል እና ጂኦፖለቲካል ጠርዞች አንፃር እየተቃኙ ተተንትነዋል፡፡ ነገር ግን ለዓባይ ውኃ 86 በመቶ ድርሻ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ባለፉት 120 ዓመታት የተነፈጋት ፍትሕ ጎልቶ ሲነሳ አይስተዋልም፡፡
ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አግላይ ውሎችን እየመዘዘች በዓባይ ውኃ ላይ “የታሪካዊ መብት ባለቤት ነኝ” ትላለች፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ ከአብራኳ የሚመነጨውን እና 86 በመቶ የውኃ ድርሻዋን ጠቅሳ በፍትሐዊነት የመጠቀም “ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብት አለኝ” የሚል መከራከሪያ አላት፡፡ በጉዳዩ ላይ የጠራ አቋም እና የለየለት አሰላለፍ የማታራምደው ሱዳን ደግሞ በነፈሰበት ስትነፍስ ማስተዋል የተለመደ ቢሆንም የመሪዎቿ ፍላጎት የፈርኦናዊያን ጃንደረቦች ከመሆን የዘለለ ግን አይደለም፡፡
የጉዳዩ ማጠንጠኛ ግን በሀገራቱ መካከል ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ይኑር ጥያቄን መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዓባይ ውኃ 86 በመቶ ድርሻ ቢኖራትም በውኃው ባለመጠቀሟ በድህነት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ለዓባይ ውኃ ምንም ድርሻ የሌላት ግብፅ ግን ውኃውን ተጠቅማ ከመልማት አልፋ 10 በመቶ የሚሆነውን ውኃ ለትነት እየመደበች የበርሃ ገነት መሆን ችላለች፡፡
በራስጌዋ 160 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የተሸከመውን የአስዋን ግድብ ገንብታ የምትጠቀም ሀገር ስለምን የዓባይ ወንዝ ማኅፀን የሆነችው ኢትዮጵያን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዳትገነባ መሰናክል መፍጠር አስፈለጋት? በየዘመኑ ብቅ የሚሉ የግብፅ መሪዎች ለኢትዮጵያ የጎን ውጋት ለምን መሆን አስፈለጋቸው?
ጉዳዩን አስመልክቶም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ውዝግብ ከፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል አለመኖር ጋር ተያይዞ መሆኑን በአሜሪካ በክላውድ እና ኤኤል ሶፍትዌር ሴኪዩሪቲ ኢንጂነሪንግ ዳይሬክተር መኮንን ካሳ (ኢንጂነር) ይገልጻሉ፡፡
የ1977 ዓ.ም ድርቅን የሚያስታውሱ ሁሉ ኢትዮጵያ ሰቆቃዊ ርሀብን እንደተጋፈጠች ሊረዳ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በሚሊዮን ሄክታር የሚለማ መሬት እያላት እንዲህ ዓይነት ሰቆቃ ልታስተናግድ የምትገደደው አማራጯ ወቅትን ጠብቆ የሚመጣ ዝናብ በመሆኑ እንደሆነ ኢንጂነር መኮንን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ጨለማ ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ ደግሞ ከ100 ቢሊዮን ዶላር አይዘልልም፤ ያልተጣጣመ አራት ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ እና 15 ቢሊዮን ዶላር የገቢ ንግድ ያላት ሀገር ፀጋዎቿን የማልማት እና የመጠቀም አማራጭ ካልፈለገች በቀር ዕድገት ፈፅሞ አይታለምም፡፡
እንደ ኢንጂነር መኮንን ሐሳብ ኢትዮጵያ አሁን የሚስተዋለውን ሀገራዊ ፈተና እና ድህነት ለመሻገር እንደታላቁ የኢትየጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነት ፕሮጀክት ከአንድ በላይ ያስፈልጋታል፡፡ በ2050 (እ.አ.አ) የኢትዮጵያ ሕዝብ 205 ሚሊዮን እንደሚደርስ ትንበያ መኖሩን ያመለከቱት ኢንጂነር መኮንን ከዚህ ውስጥ ደግሞ 50 ሚሊዮኑ ከተሜ እንደሚሆንም የትንበያ መረጃ ያሳያል ብለዋል፡፡
ይህም ዜጎችን ለከፋ የምግብ እጥረት፣ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት ችግር እና ለንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት ያጋልጣል፡፡ ዜጎች የሚገጥማቸውን ችግር ለመቋቋም ሲባል በሚወስዱት ርምጃ ደግሞ የደን መራቆት እና የተፈጥሮ ሀብት መዛባት ያጋጥማል፡፡ ይህም ሀገሪቱን እንደ 1977ቱ ዓይነት የከፋ ድርቅ እና ርሀብ በተደጋጋሚ እንዲፈትናት ላለማድረጉ ዋስትና የላትም፡፡
እንደ ኢንጂነሩ ማብራሪያ ግብፅ በቀይ ባሕር እና በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ 150 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የከርሰ ምድር ውኃ አላት፤ በተጨማሪም በታላቁ የአስዋን ግድብ ብቻ 160 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ገድባ ይዛለች፡፡ ይህን ሁሉ የተፈጥሮ ውኃ በጉያዋ የያዘችው ግብፅ
የዜጎቿን ሕይወት እና የሲናይ በርሃን እስትንፋስ የያዘችው ግን በዓባይ ውኃ ላይ ብቻ ነው፡፡
ግብጽ ይህንን የዓባይ ውኃ ዘላቂ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ ላይ የተነጣጠሩ አምስት ታሪካዊ የክልከላ መንገዶችን ትጠቀማለች ነው ያሉት ኢንጂነር መኮንን፡፡
ከአምስቱ ታሪካዊ የክልከላ ስልቶች አንዱ ከ120 ዓመታት በፊት ጀምራ በተደጋጋሚ ሞክራው ያልተሳካላት ግልፅ ጦርነት አንዱ እንደሆነ ኢንጂነር መኮንን ያነሳሉ፡፡ ሌሎቹን አራት ስልቶች ግን አሁንም ድረስ እየተጠቀመችባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የአረብ ሊግ መጫዎቻ ካርድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ውጫዊ እና ውስጣዊ አለመረጋጋትን መፍጠር፣ ብድር እና ዕርዳታ እንዳይገኝ ማድረግ እና ህቡዕና ግልፅ የጦርነት ማስፈራሪያዎች በየጊዜው ከግብፅ በኩል የሚሰነዘሩ የኢትዮጵያ መሰናክሎች ናቸው ብለውናል፡፡
በአፍሪካዊነት እና የአፍሪካ ህብረት እምነት ጥላ ለማታውቀው እና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እያየች የአሰላለፍ ለውጥ ለምታደርገው ግብፅ ጠንካራ ሕዝባዊ ህብረት እና ቁርጠኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ ያስፈልጋል ባይም ናቸው፡፡
ነገር ግን ለዓባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም የሚያመቸው መንገድ የጋራ ተጠቃሚነት እንደሆነ ኢንጂነር መኮንን ተናግረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ወቅት እያየ በሚነፍሰው የግብፅ ነፋስ ሳትወዛወዝ ግድቡን በአስፈላጊው ፍጥነት መሥራት ይጠበቅባታል” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም የውስጥ ልዩነት ቢኖርም እንኳን ልዩነትን ወደጎን በመተው በዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞች ላይ በአንድነት መቆም አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ማመን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ከሚደርስብን ጥቃት ቀድሞ ደርሶ ሊታደገን የሚችል አካል አላገኘንም” በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የአቤ ደንጎሮ ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleየእንጨት ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መዘጋጀቱን የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ገለጸ፡፡