
የጉምሩክ ኮሚሽን ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ከ3 ወር በላይ በፈጀ ኦፕሬሽን የኮንትሮባንድ እቃዎች፣ ኮንትሮባዲስቶችንና ተባባሪዎቻቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ የኮንትሮባንድ እቃዎች፣ ኮንትሮባዲስቶችንና ተባባሪዎቻቸውን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተከናወኑ ሥራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኮንትሮባዲስቱ በአዋሽ መቆጣጠሪያ ጣቢያ የፌዴራል ፖሊስ ኀላፊ የሻለቃ አዛዥ የሆነ ግለሰብን በጥቅም በመደለልና ከፌዴራል ፖሊስ አባላትና እና ከአዋሽ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሰዎችን መልምሎ እንዲያሰማራ በመመሳጠር የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቀላሉ ለማሳለፍ እየሠራ መሆኑን ጥቆማ የደረሰው የጉምሩክ ኮሚሽን ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ የኦፕሬሽን ሥራ ለ3 ወር በመሥራት የኮንትሮባንድ እቃዎች፣ ኮንትሮባንዲስቶች እና ተባባሪዎቻቸው ጭምር በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት፡፡ በዚህም 6 ሚሊዮን 196 ሺህ ብር ግታዊ ዋጋው ያለው እቃ መያዙን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት በኦፕሬሽኑ 3 የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ ዋናው ኮንትሮባንዲስት እና የኮንትሮባንድ እቃውን ሲያጓጉዝ የነበረ ሾፌር ፣ አንድ የአዋሽ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ፣ ኮንትሮባንዲስቱ እንዳይያዝ ሽፋን ሲሰጥ የነበረ አንድ የመተሃራ ፖሊስ አዛዥ ጨምሮ 7 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡ በጉቦ መልክ ሊሰጥ የነበረ 200 ሺህ ብርም እንደተያዘ አመላክተዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ሚናቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ