
የአማራ ክልልን በስድስት ወራት ብቻ ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች መጎብኘታቸውን የክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንቅስቃሴ ግን አነስተኛ መሆኑን ነው ቢሮው የገለጸው፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የላልይበላ፣ የግሸን ማርያም፣ የተድባበ ማርያም፣ የጎዜ መስጂድ፣ የአንኮበር ቤተመንግሥት፣ የዘንገና ሐይቅ፣ የጭስ ዓባይ ፏፏቴ፣ የጣና ገዳማት፣ የጎንደር አብያተ-ክርስቲያናትና ቤተ-መንግሥታት፣ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እና መሰል ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ሀብቶች መገኛ የሆነው የአማራ ክልል የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡
የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክልሉ ይህን እምቅ ሀብቱን እንዳይጠቀም አድርጎታል፡፡ ያም ሆኖ ግን ክልሉን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከታቀደው በላይ ጎብኝተውታል፡፡ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በሚበዙባቸው የደባርቅና የላልይበላ ከተሞች ተፅእኖው የጎላ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን እንቅስቃሴ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስለገታው የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን መሠረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲመጡ የተለያዬ ሁነቶችን መፍጠር አንደኛው መሆኑንም አቶ አበበ አንስተዋል፡፡
ከሸዋ እስከ ወሎ በሚል በተዘጋጀ የመስህብ ጉብኝት፣ የግሸን ማርያም ክብረ በዓል፣ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች በዓል፣ የመርቆሪዮስ በዓል፣ የጥምቀት በዓል፣ የልደትን በዓል በላልይበላ፣ የዘራ ብሩክን በዓል በግሽ ዓባይና ሌሎች በዓላትና ሁነቶች የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ እንዲመጡ ያደረጉ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ኀላፊው እንዳሉት ክልሉን በስድስት ወራት
• 6 ሚሊዮን 999 ሺህ 975 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ይጎበኛሉ ተብሎ ታቅዶ ነበር
• 7 ሚሊዮን 479 ሺህ 929 ጎብኚዎች ጎብኝተዋል
• 931 ሚሊዮን 191 ሺህ 173 ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር
• 769 ሚሊዮን 586 ሺህ 673 ብር ገቢ ተሰብስቧል፤ የጎብኚው የቆይታ ጊዜ፣ የገንዘብ አቅምና ሌሎች ምክንያቶች ለመሰብሰብ የታቀደውን የገንዘብ መጠን እንደቀነሰው አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡
• 124 ሺህ 382 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ክልሉን ይጎበኙታል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡
• 7 ሺህ 757 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብቻ በክልሉ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ይህም የኮሮናቫይረስ በውጭ ሀገር ገብኚዎች ፍሰት ላይ ያደረሰው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ነው ያመላከቱት፡፡ አቶ አበበ እንደገለጹት በክልሉ ያለውን የመስህብ ሀብት ለማስተዋወቅ ይረዳ ዘንድ በአውሮፕላን ማረፊያዎች የጎብኚዎች መረጃ ማዕከል ለማቋቋም እየተሠራ ነው፡፡
ክልሉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የሚሠራበት በመሆኑም ለቱሪዝም ፍሰቱና መነቃቃቱ የተሻለ መሆኑን ነው አቶ አበበ ያስታወቁት፡፡ በመስህብ ሥፍራዎች የኮሮናቫይረስ መከላከል ፕሮቶኮል እንዲተገበር እየተሠራ መሆኑን የተናሩት ኀላፊው በሚገባ በመተግበር ረገድ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቅሰዋል፡፡
ለጉብኝት የሚሄዱ ሰዎች ፕሮቶኮሉን በማክበር የተሻሉ ቢሆኑም በአካባቢው ማኅበረሰብ ያለው ግንዛቤ እና መዘናጋት መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር መመሪያ እንዲተገበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መቀጠላቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ