“ኦነግ ሼኔ ካቅማችን በላይ ነው እና አካባቢውን ለቅቃችሁ ውጡ ተብለናል” ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ ደቡብ ወሎ ዞን የመጡ አማራዎች

825
“ኦነግ ሼኔ ካቅማችን በላይ ነው እና አካባቢውን ለቅቃችሁ ውጡ ተብለናል” ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ ደቡብ ወሎ ዞን የመጡ አማራዎች
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን በደረሰው ዘር ተኮር ጥቃት 841 አማራዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከተፈናቃዮቹ ሴቶችና ህጻናት በዛ ያለውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ጃሪ ጊዜያዊ ማቆያ እና በሐይቅ ከተማ በሚገኘው መካነ እየሱስ ጊዜያዊ ማቆያ እንዲያርፉ ተደርጓል፡፡
ከተፈናቃዮቹ መካከል አቶ መሀመድ ጌቶ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ አጋምሳ ቀበሌ ነዋሪ ነበሩ፡፡ ተወልደው ባደጉበት ሀብት ንብረት አፍርተው የልጅ ልጅ ካዩበት መንደር ከሰሞኑ በአካባቢው በአማራ ላይ በተፈጸመው ዘር ተኮር ጥቃት ተፈናቅለው አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ይገኛሉ፡፡
እንደ አቶ መሀመድ ሁሉ 840 የአማራ ተወላጆችም ከምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ይገኛሉ፡፡ አማራ በመሆናቸው ብቻ አሰቃቂ ጥቃት ሲደርስባቸው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ለሚመለከተው አካል ቢያመለክቱም ምላሽ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም “ኦነግ ሼኔ ካቅማችን በላይ ነው እና አካባቢውን ለቅቃችሁ ውጡ ተብለናል” ብለውናል፡፡
በጊዜያዊ ማቆያው ውስጥም ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የህክምና አገልግሎት እና የቁሣቁስ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበርያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሳይ ማሩ ለተፈናቃዮቹ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ኀላፊው ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባይሆንም በቀጣይ አስፈላጊ ቁሳቁስ ለሟሟት እንደሚሰሩም ኀላፊው አቶ መሳይ ማሩ ተናግረዋል፡፡
አሚኮ ያነጋገራቸው በጃሪ ጊዜያዊ ማቆያ የሚገኙት ተፈናቃዮች የደሴ ከተማ ሕዝብ ተቀብሎ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀያት መኮነን – ተሁለደሬ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበቲቢ በሽታ የመያዝ መጠንን በ90 በመቶና የመሞት መጠንን በ95 በመቶ ለመቀነስ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡
Next article“የምናስተውላቸው ሀገራዊ ፈተናዎች እንደ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብም መውረዳችንን አመላካቾች ናቸው፡፡” ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ