ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ትክክለኛ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓተ ጽሕፈትን በመጠቀም ሕዝብን ሊያስተምሩ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡

533

ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ትክክለኛ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓተ ጽሕፈትን በመጠቀም ሕዝብን ሊያስተምሩ እንደሚገባ
ምሁራን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአማርኛ ቋንቋ የዘገባ ሥራዎችና የጽሕፈት ተግባቦት
ላይ ትክክለኛ የቋንቋ ሥርዓተ ጽሕፈት ለመከተል የሚያስችል የቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ በማዘጋጀት ከሠራተኞች፣ ከባህልና
ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለተወጣጡ ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
ሥልጠናው የአሚኮ ሠራተኞች በዘገባዎቻቸው ለማኅብረሰቡ አግልግሎት ሲሰጡ የትርጉም ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሞክሼ
ፊደላትን፣ የተለየ ብዜት ያላቸው ቃላትን፣ የሙያ ቃላትንና መሰል ተግባራትን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤ ለመፍጠር
የተዘጋጀ ነው፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል ጋዜጠኛ አባትሁን ዘገየ እንደገለጸው በአማርኛ ቋንቋ አጻጻፍ ብቻ ሳይሆን በንግግር ላይም የከፋ ችግር
እየታየ ነው፡፡ በመሆኑም በአንድ ጊዜ ከብዙ ሚሊዮን የሕዝብ ጆሮና ዐይን የሚደርሱ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የአማርኛ ቋንቋ
አጠቃቀም እንዲስተካከል ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡
የተሠጠው ሥልጠናም እየታዩ ያሉ የቋንቋ አጠቃቀም ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን አመላክቷል፡፡ “የቋንቋ ሊቃውንት
ቋንቋን የፈጠሩት በምክንያት ነው” ያለው ጋዜጠኛ አባትሁን አሚኮም በማኅበራዊ ትስስር ገጽ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና ጋዜጦች
ልዩ ሽፋን በመስጠት እየጠፋ ያለውን የቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓት ሊታደግ እንደሚገባው አስረድቷል፡፡
በሥልጠናው የተሳተፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግእዝ መምህር ዕጩ ዶክተር አባ በአማን ግሩም ‹‹ቋንቋ የሐሳብ መግለጫ
የአንድ ሕዝብ ሀብት ነው›› ብለዋል፡፡ የሕዝብ የሆነው አሚኮም የቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ ሥልጠና
መስጠቱ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በርካታ የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶችም በጽሕፈት ዘርፍ በሚተላለፉ መልእክቶች ላይ ትክክለኛውን ፊደል የመጠቀም
ችግር እንደሚታይባቸው መገንዘባቸውን አስረድተዋል፡፡ በአሚኮ የቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ ተግባራዊ መደረጉም ለሕዝቡ
የሚተላለፈው መልእክት ትክክለኛውን ሐሳብ ይዞ እንዲተላለፉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በቋንቋ አጠቃቀም ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት “የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣
የሃይማኖት አባቶች፣ የቋንቋ ፖሊሲ አውጪዎችና የሥራ ኃላፊዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል፡፡
በአሚኮ የሥልጠናና ምርምር ማእከል ምክትል ዳይሬክተር አብርሃም በዕውቀት እንደገለጸው በተቋሙ ግልፅ የሆነ ተግባቦት
ለመፍጠር ሁሉም ተመሳሳይ ቃላትን በተመሳሳይ ፊደል እንዲጠቀም የቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየሆነ
ነው፡፡
የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም መመሪያውም ነባር የአጻጻፍ ሥርዓት እንዲጠበቅና በፊደል ልዩነት የሚፈጠረውን የትርጉም ለውጥ
ለማስተካከል እገዛ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግሯል፡፡
‹‹የአማርኛ ቋንቋ የዳበረ ሥርዓተ ጽሕፈት ኖሮት አንዲጓዝ እንደብዙኃን መገናኛ ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል›› ሲልም
አብራርቷል፡፡ በብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለው ችግር መስተካከል እንደሚገባቸውም
መልእክት አስተላልፏል፡፡
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ተግባራዊ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን መከላከል እንደሚገባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመኖሪያ አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የባሕር ዳር ቅርንጫፍ አስተባባሪ ገለጹ፡፡
Next articleበቲቢ በሽታ የመያዝ መጠንን በ90 በመቶና የመሞት መጠንን በ95 በመቶ ለመቀነስ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡