
ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ እስካሁን 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብስብ መቻሉን ዶክተር ሲለሺ በቀለ ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ የሕዳሴ ግድቡን 10ኛ ዓመት በማስመልት እንዳሉት ዓመቱ ወሳኝ የሆኑ ሥራዎች የሚሠሩበት ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠራው ሥራ የግድቡ አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 79 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡ በዓመቱ የግድቡ የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች የሚሠሩበት ዓመት ነውም ብለዋል፡፡ ተጨማሪ 11 ተርባይነሮችን ማንሳት የሚችሉ የብረት ሥራዎች እየተሠሩ ነውም ብለዋል፡፡ ዓመቱ የግደቡን ቁመት ለማሳደግ የኮንክሪት ሥራ የሚከናወንበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለግድቡ እስከአሁን ድረስ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድና በቀጥታ ድጋፍ መበርከቱንም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት እስከአሁን ድረስ ብቻ 1 ነጥብ 48 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሚሰጡት ትርጉም ከፍ ያለ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ግድቡ ኢትዮጵያን ከድህነት በማውጣት ወደ እድገት የምትሄድበትን መሠረት የሚጥል ነውም ብለዋል፡፡ በቀሪዎቹ ጥቂት ወራት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት የታቀደውን የሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ተርባይነሮች ኃይል የማመንጨት ሥራው እንዲሳካ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገፅ በምስል ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት የድርድሩ ጉዳዩም በተያዘለት ጊዜ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ምንጊዜውም ፍትኃዊ በሆነ ተጠቃሚነት አካሄዷ ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለግድቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥልና የምናልመውን እንደናሳካ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡ በግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪነት ዛሬና ነገ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ