
“አብቁተ በክልሉ ሥር የሰደደ ድህነትን ለመዋጋትና ልማትን እውን ለማድረግ የተመሠረተ የፋይናንስ ተቋም ነው” የአብቁተ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መኮንን የለውምወሰን
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ እንዲሸጋገር ከባለ አክስዮኖች ጋር በባሕር ዳር ውይይት እያደረገ ነው፡፡ አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) በክልሉ ሥር የሰደደ ድህነትን ለመዋጋትና ልማትንና ብልጽግናን እውን ለማድረግ የተመሠረተ የፋይናንስ ተቋም መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መኮንን የለውምወሰን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ያለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር ተወግዶ ኅብረተሰቡ የተሻለ ሕይወት እንዲመራ ጠንክሮ የሚንቀሳቀስ ተቋም መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስረድተዋል፡፡
በፋይናንስ ሥርዓቱ ከፍተኛ የገበያ ጉድለት በሀገርና በክልል መሠረታዊ ችግር ሆኖ በመከሰቱ መንግሥት ኀላፊነቱን ወስዶ ተቋሙ እንዲቋቋም እንዳስቻለው አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡
አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከመቋቋሙ በፊት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖችና በተመረጡ 29 ወረዳዎች ጥናት አካሂዶ እንደነበር ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል፡፡ በጥናቱ መሠረትም ድሃው የኅብረተሰብ ክፍል አነስተኛ የብድር አገልግሎትን እንደ እድገት መሣሪያ ተጠቅሞ የማደግ ፍላጎት እንዳለው መረጋገጡንም ጠቁመዋል፡፡ ሌላ አማራጭ የፋይናንስ መስጫ ሥርዓት እንደሚያስፈልግም ጥናቱ እንዳመላከተ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
አማራጭ ሥርዓት ለመዘርጋትም የውጪ ሀገራት ተሞክሮ ከማኅበረሰባችን የፋይናንስ አገልግሎት ልምዶች ጋር በማስተሳሰርና በመቀመር አዲስ የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደተቻለ አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ሲመሠረት ከውጪ ሀገራት ልምድና ተሞክሮን በመቀመር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ1988 ዓ.ም የሙከራ ሥራውን ሲጀምር በ1989 ዓ.ም በወጣው አዲስ የማይክሮ ፋይናንስ ሕግ መሰረት የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ማይክሮ ፋይናንስ ሆኖ መቋቋሙንም አስታውሰዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትና አራት የክልሉ የልማት ድርጅቶች በድምሩ አምስት የባለአክስዮን ማኅበር አባላት በባለቤትነት ተመዝግበው የክልሉ ሕዝብ ተቋም በመሆን መመሥረት እንደቻለም አመላክተዋል፡፡
ተቋሙ ሥራውን የጀመረው በ 3 ሚሊዮን ብር እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም ቁጥራቸው በርካታ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከድህነትና ከጉስቁልና ሕይወት ሊላቀቁ እንደቻሉ አቶ መኮንን አረጋግጠዋል፡፡
አብቁተ
• አሁን ላይ 471 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣
• 1 ሺህ 107 ሳተላይት ጽሕፈት ቤቶች
• 12 ሺህ 680 ሠራተኞች፣
• 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የብድር ደንበኞች፣
• 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቆጣቢዎች እንዲሁም
• 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታልና
• 36 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት እንዳለው አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ