ʺእንደ ነበረ አይኖር ሁሉም ይለወጣል
የእነርሱ ቀን ሲመሽ ያንተ ቀን ይወጣል…”
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የግፍ እንባዎች ይፈሳሉ፣ ደራሽ ያጡ ምስኪኖች ይጮኻሉ፤ መሞት ሲሆን
ለአማራ፣ መዳን ሲሆን ለጋራ ሆኗል ነገሩ፣ አማራ ለሠንደቁ ክብር፣ ለሀገሩ ፍቅር ሲል መሪር ሞትን ይቀምሳል፤ የከፋ መከራን
ይታገሳል፡፡ አማራ ሠውን በሰውነቱ ይመዝናል፣ ለወዳጁ ያዝናል፣ ጠላቱን ልብ እንዲሰጥለት ፈጣሪውን ይማፀናል፤ ይህን ሁሉ
አልፎ ሀገርህን፣ ርስትህንና ሚስትህን ልንጠቅህ ሲሉት ግን ያመቀው ትዕግስቱ፣ የሚጎመዝዘው ኃይለኛ ሀሞቱ ይመጡበታል፡፡
ያን ጊዜ ጠላቱን አያደርግ፡፡
አማራ ብልህ ነው በብልሃት ይፈርዳል፣ ፈጣሪውን አክባሪ ነው ለፈጣሪው ይሰግዳል፣ ጥበበኛ ነው በጥበብ ይራመዳል፣ የዋህ ነው
እንግዳን ከአልጋ አስተኝቶ እርሱ ወደ ወለል ይወርዳል፤ ጀግና ነው ቁጣው የጠላትን ልብ ያርዳል፣ የተቆለለን የመከራ ቋጥኝ
ይንዳል፡፡ ስለ ሀገሩ ኢትዮጵያ ይሞታል፡፡ ስለ ፍትህ ይሟገታል፡፡
ʺየፈለጉት ነገር እንደ ልብ አይገኝ
እምዬ ኢትዮጵያ ከአንቺ በፊት ያርገኝ” እንዳለ ከያኙ አማራ እኔን ከኢትዮጵያ በፊት ያድርገኝ እያለ ስለ ኢትዮጵያ መስዋዕት
ይሆናል፡፡ በጽናቱ፣ በመስዋዕትነቱ፣ በአንድነቱ፣ በሃይማኖቱና በጀግንነቱ ብዙዎች ሲገረሙ ብዙዎች ደግሞ ይበሳጫሉ፡፡ እንዴትስ
ከክብሩ እንዋርደው፣ እንዴትስ አንገቱን አስደፍተን እናስሄደው ይላሉ፡፡ ዳሩ በዘመናት ቅብብሎሽ መፈተን የለመደው ነውና
ፈተናዎቹን እያለፈ፣ ሊያወርዱት ያሰቡትን እያወረደ፣ በጨለማ እናኑረው ያሉትን የብርሃን ጎህ እየቀደደ በአሸናፊነት ይጓዛል፡፡
በሰፋች ሀገር አልጠብም፣ በቀደመች ዓለም ወደኃላ አልመለሰም፤ ሁሉም ሀገሬ፣ ሁሉም ወገኔ በማለቱ መከራው በዝቶበታል፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ከጫፍ እስከ ጫፍ መኖር የኢትዮጵያውያን ነው ብሎም ያምናል – አማራ፡፡ ታዲያ መከራዎች በዙበት፡፡
እየገደሉት ተው ስለ ኢትዮጵያ ስንል ሞት አይበጅም ይላል፡፡ እነርሱ ያነሱትን ያነሳ ቀን ምድር ወና እንደሆነች ያውቀዋልና፤ ከሞቱ
በላይ የሀገሩ መጻዒ እድል ያሳስበዋል፡፡ በፈጣሪውና በሀገሩ ተስፋ አይቆርጥምና ጊዜን ጊዜ ይሽረዋል፣ ሰው ያልመከረውን
ሕይወት ይመክረዋል እያለ ትዕግስትን ያስቀድማል፡፡ የልቦናው ስፋት ግሩም ነው፡፡
አማራ በየዘመናቱ ዘመንን እየዋጀ ታሪክ ሠሪ፣ ታሪክ ዘካሪ፣ እውነት መስካሪ፣ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለወገን ኗሪ ነው፡፡ ከነብሱ
አስበልጦ የሚወዳት ሀገሩ፣ አብዝቶ የሚወደው ወገኑ በተነካበት ቁጥር ʺ እንብኝ አሻፈረኝ ” እያለ ሲዋደቅ፣ የተተበተበን የመከራ
ድር ሲያላቅቅ፣ ከጠላት ጋር ሲተናነቅ የኖረ ሕዝብ ነው አማራ፡፡ ጣልነው ሲሉት የሚነሳ፣ አጠፋነው ሲሉት የሚያገሳ፣ ረታነው ሲሉት
መትቶ እጅ የሚያስነሳ፣ እየሞተ የሚበዛ፣ በግርማ፣ በጥበብ፣ በእውነት፣ በአንድነት የሚገዛም ነው – አማራ ፡፡ ገዳዮቹ
በርክተዋል፡፡ ጠላቶቹ እንደ አሸን በዝተዋል፡፡ ያም ሆኖ እንደሚያሸንፋቸው ያምናል፤ ያሸንፋቸዋልም፡፡
ደራሲ አበረ አዳሙ እንዲህ በል ይለኛል በሚል የግጥም ርእስ በአንድ መድረክ ላይ የተቀኙትን ግጥም አስታወሰኝ፤ ትንሽ ስንኞች
መርጬ ወሰድኩ፤
ʺ ሀገራችን ሌላ ያለን በሰው ሀገር
ዛፍ ያነቃንቃል የምንሰማው ነገር
አልንበረከክ ባልኩ ተኩሰው ሊመቱኝ አውሬ መስያቸው
ከሰው መወለዴን ኢትዮጵያዊነቴን ማን በነገራቸው፡፡
እንደነበረ አይኖር ሁሉም ይለዋጣል
የእነርሱ ቀን ሲመሽ ያንተ ቀን ይወጣል
ያንተ እድል ሲሞላ የእነርሱ ያጥጣል
ግፍ እኮ ሲበዛ እግዜሩ ይቆጣል
ኃያሉን ያደክማል ቀጥቃጩን ይቀጣል…”
እኒሁ ደራሲ አበረ አዳሙ በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ቦታዎች ደማቸው ሲለሚፈሰው፣ አጥንታቸው ስለሚከሰከሰው፣ በግፍ ስጋቸው
ስለሚቆረሰው አማራዎች በተመለከተ ጠላቶች ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በምስራቅ አፍሪካ እንዳትኖር የማድረግና አማራው
በእልህ ተነሳስቶ ተመሳሳይ ጥፋት እንዲፈፅም ይፈልጋሉ፡፡ አማራ በተገኘበት ሁሉ እንዲሰደድ የተወሰነበት ይመስላል፣ ኢትዮጵያን
እንዳልነበረች የማድረግ ዓላማ የያዙ ይመስላል ነው ያሉኝ፡፡
በአንድ ወቅት በሀገረ ግብጽ የገጠማቸውን ሲነግሩኝ ʺ የሀገሪቱ ታላላቅ ባለስልጣናት የታደሙበት አንድ ትልቅ ስብሰባ ነበር፡፡
በወቅቱ የነበሩ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ የዓባይን ግድብ መገደብ ጀምራለች፤ ስለዚህ በጦር ማንበርከክ
አለብን፡፡ የኢትዮጵያን አቅምም ማሳዬት አለብን የሚል ሀሳብ ሰነዘሩ፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ ፕሮፌሰር ተነሱና አላህ ከእናንተ
ከጨቅላዎች እጅ ላይ ሀገሬን ሲጥላት ሳላይ ብሞት ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን እኮ የተፈጠሩት ለጦርነት ነው፡፡
እየጨፈሩ መጥተው አይደለም የሀገራቸውን ድንበር ማስከበር ይቅርና የአስዋንን ግድብ ብትንትኑን ያወጡታል፡፡ ሌላ ዘዴ ነው
መቀየስ ያለብህ፡፡ እርሱም ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቋንቋና ባሕል ያላቸው ሕዝቦች ስላሉባት ያኮረፉትን እየመለመሉ ወደ አማፂነት
እንዲገቡ ድጋፍ እየሰጡ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ማድረግ አንደኛው ስልት ይሆናል፡፡ ይህ የማያዋጣ ከሆነ ግን በኢንቨስትመንት
ስም እየገቡ ስንዴን በኢትዮጵያ እያመረቱ ወደ ግብጽ ማስገባት ሌላኛው ስልት ነው” አሉ አሉኝ ፡፡ ግብጽ በቀጥታ ጦርነት
እንደማትከፍትና ኢትዮጵያን እንደማትገጥም የኢትዮጵያ ሕዝብ መረዳት እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ነገር ግን በጀርባ በኩል
እየገባች ሀገሪቱ ሰላም እንዳትሆን ትሠራለች ነው ያሉኝ፡፡
አሸባሪው አይ ኤስ አይ ኤስ ሰው ሲገድል ፊቱን ይሸፍናል በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ግን የጭካኔያቸው ጭካኔ ህጻን ገድለው ፎቶ
ተነስተው ለሕዝብ ያሳያሉ ነው ያሉት፡፡ የጥፋተኞቹ ዓላማ አማራን መግደል ብቻ ሳይሆን ሀገርን ማፍረስ ነውም ብለዋል፡፡ አማራ
ደግሞ በኢትዮጵያዊነቱ ስለሚታወቅ አማራን ከገደልኩ ኢትዮጵያን አፈረስኩ የሚል ዓላማ ሳይኖራቸው እንዳልቀረም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የተሳሰሩበት እሴት ጠንካራ መሆኑ እንጂ አማራው ሲገደል ተነስቶ ሌላኛውን እንዲገድል ማድረግ ዓለማቸው
መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከልማት በፊት የሰው ሕይወት መቅደም አለበትም ያሉት ደራሲው እየደረሰ ባለው ግድያ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች
እንቅልፍ ሊያጡ፣ ሊያፍሩም ሊፈሩም ይገባልም ብለዋል፡፡ ሰው በግፍ እየተገደለ ያለው ከእነርሱ ክልል ነው፣ ሕዝብን የመጠበቅ
ግዴታ አለባቸው፣ የመጀመሪያ ተጠያቂዎችም ናቸው፣ ቀጥሎ የፌዴራል መንግሥትም ዜጎቹን መጠበቅ አለበት ኃላፊነትም አለበት
ነው ያሉት፡፡
“የፖለቲካ ፍላጎት ያለው ቡድን ፍላጎቱ ከፖለቲከኞች ጋር እንጂ ከንጹሐን ጋር አይሆንም” ያሉት ደራሲ አበረ አዳሙ ንጹሐን
ስልጣን አይጋፉ፣ ነጻ አውጭ ነኝ የሚል ካለ ከፖለቲከኞች ጋር እንጂ ከንጹሐን ጋር ምን አገባው ነው ያሉት፡፡ ሁልጊዜም ታጣቂና
ነጻ አውጭ ነው የገደላቸው ከማለት ክልሎች በየጊዜው የሚሰለጥነው የጸጥታ ኃይል ምን እየሠራ ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ የመሪዎቹ እጅ ካለበት እኛም አለንበት ብሎ በግልፅ መናገር ካልሆነ ግን መብታቸውን አስጠብቆና ጠብቆ የማኖር
ግዴታ አለበትም ብለዋል፡፡ በየቀኑ ሰው እያስገድሉ ያሉ የክልል መሪዎች መቀጠል የለባቸውም፤ መጠየቅ አለባቸውም ብለዋል፡፡
ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ ያለው አካል መጠየቅ አለበትም ነው ያሉት፡፡ ʺጸጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” እንዲሉ በዚህ
ከቀጠለ ዛሬ ምንም አይሆኑም የሚባሉ አካባቢዎች የችግሩ ሰለባ መሆናቸው አይቀርምም ይላሉ ደራሲው፡፡
የመገናኛ ብዙኃን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎችም ለፍትሕ መቆምና መጮኽ አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ትህነግ የሠራው ሥራ በጊዜ እልባት ቢሰጠው ኖሮ ችግሩ የከፋ ባልሆነ ነበር ያሉት ደራሲው አሁን ያለው አካሄድ በእንጩጩ
መቀጨት አለበትም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጠ መዘዝና የከፋ ችግር ሳይመጣ መጮኽና ከሚመለከተው አካል ጆሮ
ማድረስ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ ደምና አጥንት የተገነባች ሀገር ናት፣ ቀልድ አይደለችም፣ ኢትዮጵያ ከፍ እንድትል ንጹሐንን መግደል መቆም
አለበት፣ ንጹሐንን መግደል ግለስብን መግደል ብቻ ሳይሆን ሀገርንም መግደል ነው፣ የፖለቲከኞች እብደት ሀገርን እያሳበዳት ነው፣
ፖለቲከኞች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ሕዝቡንም ሊታደጉ እነርሱንም ሊያድኑ ይገባል፣ ግፍ ሲበዛ ይፈሳል፣ ጎበዞች ከሆኑ
ሀሳባቸውን ይንገሩን ምርጫ እየመጣ ነው እንምረጣቸው፣ በጠመንጃ የሚመጣ ስልጣን በጠመንጃ ይወርዳል፣ ካለፈው ታሪክ
መማር አለባቸውም ብለዋል ደራሲው፡፡
እስከሚያልፍ ሊያለፋ ይችል ይሆናል እንጂ ቀኑ ያልፋል ያሉት ደራሲ አበረ አዳሙ በትዕግስትና በጥበብ ለማለፍ አንድነት
ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ “አማራን እርስ በእርሱ ለማጨራረስና ያለ መሪ ለማስቀረት የሚደረግ ተንኮል አለ፣ ሕዝቡ አሁን መሪዎቹን
ማገዝ መቻል አለበት” ነው ያሉት፡፡
አማራን ለመከፋፈል ሊከፍቱት የሚፈልጉትን በር እንዲከፍቱት መፍቀድ አይገባምም፣ በሩ በጥንካሬ መዘጋት አለበትም ብለዋል፡፡
ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ጥበብ የተመላበት ግንኙነት ሊኖር ይገባልም ብለዋል፡፡ የአማራ መሪዎችና ሕዝቡ ከመቼውም
ጊዜ በላይ አንድነታቸውን ማጠንከር እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
የበዮች አለመስማማት ለተበዮች ይመቻል እንደተባለ አማራ በተከፋፈለ ቁጥር ለበዮች እየተመቻቸና ንጹሐንን እያስበላ ነው
የሚሄደው ነው ያሉት፡፡ በምንም ጉዳይ ተስፋ መቆረጥ እንደማይገባና የሚመጣውንም ነገር እንደ አመጣጡ በልኩ መቀበል
እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
እኔም እላለሁ በፈተና ጊዜ ጠንካራ ሆኖ ጠላቶችን ማሳፈር እንጂ፣ ሆደ ባሻ ሆኖ ማቀርቀር አይገባም፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m