በቀጣይ ቀናት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደገና እንደሚጀመር የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

388
በቀጣይ ቀናት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደገና እንደሚጀመር የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር፣ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገፃቸው “ለመላው ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 10ኛ ዓመት እንኳን አደረሰን፤ ግድብዎ አሁን 79 በመቶ ተጠናቋል” ብለዋል፡፡
“ውኃውን ሠላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ቁርጠኛ ነን፤ ለግድቡ የምናደርገውን ድጋፍ በማጠናከር ለሠላም ያለንን ቁርጠኝነት እንቀጥላለን፡፡” ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብጽ የሦስትዮሽ ውይይት በመጪው ቅዳሜና እሁድ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት የሚጀመር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የውኃ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ሚኒስትሮች ጥሪ ተደርጎላቸዋል ብለዋል፡፡
በድርድሩ የአፍሪካ ኅብረት ኤክስፐርቶች፣ ታዛቢዎች እና የሀገራቱ ባለሙያዎችም ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ዓባይ ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሃብት መሆኑን እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ድርቅ፣ ጎርፍ እና መሰል አሉታዊ ተፅእኖዎችን ይቀንሳል፤ ውድ የሆነውን የውኃ ሀብት ለማልማትና የተሻለ አያያዝ እንዲኖር አዎንታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የጎላ ተፅእኖ በማይኖረው መልኩ ኢትዮጵያ እንደወትሮው በመርህ ላይ የተመሠረተ፣ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህን እንደምትከተልም ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሰለሺ በቀለ አስረድተዋል፡፡ ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአማራ ላይ የሚፈጸመውን ግድያ የፌደራል መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር አሳሰቡ፡፡
Next articleበኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ላይ በደረሰ ስርቆት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡