
በምዕራብ ወለጋ ባቦ ገንቤል ወረዳ በቂ የሆነ የጸጥታ ኃይል ባለመሰማራቱ በአካባቢው ውጥረት መኖሩን ከጥቃቱ የተረፉ አማራዎች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ አካባቢ በተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በርካታ አማራዎች ህይዎታቸው አልፏል፡፡
ይህን ዘገባ እስከምናጠናቅርበት ጊዜ ድረስም የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተፈፀመ እንደነበር ከጥቃቱ የተረፉ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ከተፈፀመው ጭፍጨፋ በኋላ በአካባቢው ውጥረት ነግሶ እንዳደረ የነገሩን አስተያየት ሰጭዎቹ የአካባቢው ማኅበረሰብ በአንድ አካባቢ ተሰባስቦ በስጋት ሌሊቱን አሳልፏል ነው ያሉት፡፡
የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኀይል በአካባቢው ቢኖርም ቁጥራቸው ውስን በመሆኑ የሕዝቡን ስጋት የሚቀርፉ አይደሉም ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፡፡
በአካባቢው የሽብርተኛው ቡድን ሙሉ በሙሉ እስካልፀዳ ድረስ ስጋቱ በዘላቂነት ሊቀረፍ እንደማይችልም ነው የተናገሩት፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት የሰጠው መግለጫ አሳዝኖናል ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ የሟቾች ቁጥር በተዛባ መልኩ ከመቅረቡ ባለፈ ሙሉ በሙሉ የጥቃቱ ሰለባ አማራዎች ሆነው ሳለ ነገሩን ለማድበስበስ የተሄደበት መንገድ ከዚህ በኋላም መፍትሄ እንደማይኖረው አመላካች ነው ብለዋል፡፡
በኦነግ ሸኔ ላይ ተወሰደ የሚባለው እርምጃም በአካባቢው ማኅበረሰብ ዓይን ያልታየ እና ማስተባበያ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ግድያ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች የተረፉ ዜጎች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል ያሉት አስተያየት ሰጭዎች ከደረሰባቸው ስብራት አገግመው በቀጣይ ህይዎታቸው ዙሪያ መወሰን እስኪችሉ ድረስ በቂ የጸጥታ ኀይል ወደ አካባቢው እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ:— ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ