
በመተከል ዞን የሚገኙ ነዋሪዎች ዛሬም በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ትናንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ጂግዳ ቀበሌ ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ ሲጓዝ በነበረ መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ በነበሩ ተጓዦች ላይ ግድያ እንደተፈጸመ አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ስለ ዛሬ አዳራቸው የጠየቅናቸው ነዋሪዎች ‹‹ማታ ላይ ከፍተኛ ተኩስ ነበረ፤ አሁንም ስጋት ውስጥ ነው ያለነው፤ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴም የለም›› ብለዋል፡፡
በወረዳው የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ በመግባት አካባቢውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
“አሁንም ቢሆን የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ለማድረስ ወደ ጫካ ገብተዋል፡፡ በመተከል ዞን በተደጋጋሚ በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሊቆም ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ነዋሪዎቹ በአሁኑ ሰዓት በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ሠራዊት እየተጠበቁ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ዘወትር ዘርን መሠረት አድርገው የንጽሐንን ሕይወት የሚቀጥፉ የጥፋት ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ