
የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ሕዝቡን እንዲያወያዩና ጥፋተኞችም በሕግ እንዲጠየቁ የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝቡን መልካም ግንኙነት ለማጠልሸት የሚደረግ እንቅስቃሴ ጊዜው ያለፈበት፣ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ሕዝቡን የማይጠቅምና ማኅበራዊ መሠረት የሌለው መሆኑን የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከሚሴ ስትነሳ ፍቅር፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ መከባበር፣ እና ብዝኀነት ይታሰባሉ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በብሔር፣ በሃይማኖት ወይንም በሌላ ከፋፋይ አጀንዳ የማይናወጥ ጠንካራ የስነልቦና ውቅር አላቸው፤ የሕዝቡ የአብሮነት ዕሴትም ዘመናትን የተሻገረ እና የዳበረ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ መሰረት አለው።
ሕዝቡ በሰላምና በፍቅር እንደሚኖር ቢታወቅም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ አለመተማመን እንዲፈጠርና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከት እየተሠራ ነው፤ ለዚህም ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድድ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማሳያ ነው። የጸጥታ ችግሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ባይገልጽም በንጹኀን ላይ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ቀውስ ደርሷል ብለዋል።
አህመድ እንድሪስ የተባለ የከተማው ወጣት “ከሚሴ በፌስቡክ እንደሚነዛው ሳይሆን በመሐባ የሚኖርባት የፍቅር ከተማ ናት” ብሏል። የጸጥታ ችግሩ በመልካም ግንኙነት ላይ የተመሠረተውን የአማራ እና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ግንኙነት ለማጠልሸት የተሠራ የፖለቲካ አሻጥር መሆኑንም ተናግሯል።
ትህነግ ሁለቱን ብሔር ለማጋጨት ለዓመታት ሲሠራ እንደነበርም ገልጿል፣ አሁንም ከፋፋይ አጀንዳ ወደ ሕዝቡ እየተሠራጨ እንደሆነ ጠቅሷል። ይህንን ተቋቁመው የአማራና የኦሮሞ ሕዝብና መንግሥት ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ያመጡትን ለውጥ በጋራ ማስቀጠል እንዳለባቸው ነው ወጣቱ የተናገረው።
በጸጥታ ችግሩ ከደረሰው ኪሳራ ትምሕርት በመውሰድ ለቀጣይ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባም አንስቷል። ለዚህም የአማራ ክልል መሪዎች ሕዝቡን ማወያየት አለባቸው ነው ያለው። ብዙ ኪሣራ የደረሰበት ችግር ችላ ሊባል እንደማይገባም የተናገረው አህመድ “ምርጫው ሳይደርስ የክልላችን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ሕዝቡን አወያይተው፣ የተፈጠረውን ችግር መፍታት አንደሚገባቸው፣ ጥፋተኞችም በሕግ ሊጠየቁ ይገባል” ብሏል።
የመንግሥትና የሕዝብ ትኩረት የኑሮ ውድነትን መቀልበስ እንዲሁም ድህነትን እና ኋላቀርነትን መዋጋት ሊሆን እንደሚገባ አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ለዚህም አስተማማኝ ሰላምን የሚያስቀጥል ርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል። በሰው ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደል እና ንብረት ውድመት የሚያተርፉ የፖለቲካ ቁማርተኞችና ከፋፋይ መገናኛ ብዙኀንም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በከሚሴ ከተማ ከመጋቢት 12/2013 ዓ.ም ጀምሮ የጸጥታ ችግር ተከስቶ ነበር። አሁን በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል። ሕዝቡም ወደ መደበኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው መመለሱን የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በአካል ተመልክቷል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ —ከከሚሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ