በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 8 ሺህ ሲጠጋ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ200 ሺህ አልፏል፡፡

110

በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 8 ሺህ ሲጠጋ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ200 ሺህ አልፏል፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከታወቀ አንድ አመት አልፎታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ለ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

እስካሁን 154 ሺህ 323 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ አገግመዋል። በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 7 ሺህ 250 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 769 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ 805 ግለሰቦች ደግሞ በፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እየታከሙ ይገኛሉ።

ከዚህም ባለፈ ኮሮና ቫይረስ እስካሁን በ2 ሺኀ 801 ሰዎች ላይ ሞትን፤ በቀሪው ማኀበረሰብ ላይ ደግሞ ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስን አስከትሏል።

በአማራ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል፣ መቆጣጠር፣ ምላሽ መስጠት እና መልሶ ማቋቋም ባለሙያ ተመስገን አንተየ እንዳሉት በአማራ ክልል እስከ መጋቢት 20/2013 ዓ.ም ድረስ
• ለ255 ሺህ 828 ሰዎች ምርመራ ተደርጓል
• 7 ሺህ 930 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል
• 152 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡
የክልሉ የኮሮና ቫይረስ የሞት መጠንም 2 በመቶ ሲሆን ከፌዴራሉ በዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ብልጫ አለው፡፡

አጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ሲሆን ምሥራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ይከተላሉ፡፡ ባለፉት አራት ወራትም ቫይረሱ እየጨመረ እንደሚገኝ አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው እንዳሉት ለቫይረሱ መጨመር ጥናት ቢጠይቅም የቫይረሱ መከላከያ መንገዶችን አለመጠቀም እንደምክንያት ተቀምጧል፡፡ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ መጫን፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የጥንቃቄ ጉድለት ለችግሩ መስፋት የራሱን ሚና እየተጫወተ እንደሆነም ነግረውናል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች ጭምር በዘመቻ ይሰጥ የነበረው ምርመራ በመቆሙ የክልሉ የመመርመር አቅም መዳከሙንም ገልጸውልናል፡፡ በዚህ ወቅትም በባሕርዳር ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሆስፒታል፣ በደብረ ማርቆስ፣ በእንጅባራ፣ በደብረ ብርሃንና በደሴ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ምርመራ ያቆሙ እንደ ወሎ፣ ወልድያ እና ጎንደር የመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ምርመራ እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ነግረውናል፡፡

የጤና ሚኒስቴር እና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ያወጡትን መመሪያ ለመተግበርም ቀደም ብሎ ተቋቁሞ የነበረው ኮማንድ ፖስት እና በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ማሕበረሰቡም ከመዘናጋት በመውጣት እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መግታት ይገባዋል ብለዋል፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል አገልግሎት መስጫ ተቋማትም የኮሮናቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር እና የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቫይረሱን ለመግታት በሰዎች እንቅስቃሴና ማኀበራዊ ተግባራት ላይ ክልከላ የሚጥልና በወንጀል የሚያስጠይቅ መመሪያ መጋቢት 18/2013 ዓ.ም በማውጣት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኦሎሞፒክ ኮሚቴው ያደረገው ምርጫ ሕገ ወጥ እንደሆነ አስታወቀ።
Next articleበሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡