
“ያለ ሰላም ሀገር ትርጉም አልባ መሆኗን በመረዳት ሁሉም ለምርጫው ሰላማዊነት ድርሻውን ይወጣ” ኡስታዝ አቡበከር አህመድ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ያለሰላም ሀገር ትርጉም አልባ መሆኗን ከሶርያና ከየመን ሕዝብ ስደትና መከራ በመማር ሁሉም የዘንድሮውን ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ጥሪ አቀረቡ።
ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በምርጫ ሰላማዊነት ዙሪያ እንዳስታወቁት፣ የሃይማኖት አባቶች አሁን ያለውን የተሻለ የእምነት ነፃነት በመጠቀም በአመለካከቱ በሰላም የተቃኘ ዜጋ እንዲሆን ምእመናኑ ላይ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ሀገርና ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። በኢኮኖሚ ከእኛ የተሻሉ ግን ደግሞ መረጋጋት ጠፍቶባቸው፣ ሁሉም ነገር ተበለሻሽቶባቸው ተዋርደው ጠያቂና ፈላጊ ሆነው በግራ መጋባት ውስጥ የሚማቅቁ አንዳንድ ሀገሮች ስንመለከት፣ ሰላም ለአንድ ሀገር ምን ያህል ዋጋ እንዳለውና ያለ ሰላም ሁሉም ከንቱ መሆኑን ያስ ተምረናል።
«ሕዝባችን በአመዛኙ ሃይማኖተኛ በሆነው አገር፣ የሰላም ነገር በደንብ ይገባናል» ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፣ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናየው እንዲያውም ሃይማኖተኛ ካልሆኑት እንኳ የማይጠበቁ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ ጸያፍ ተግባሮችና አስተሳሰቦች በጅምሩ ለመቅጨት ሕዝቡ በተለይ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም እጦት ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሁሉንም በር እያንኳኳ ነው ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፣ ነገሮችን በጥንቃቄ ማየት ከተቻለ ችግሮቹ በቀላሉ ሊቀረፉ ይችላሉ ብለዋል።
ከዚህ በፊት በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ምክንያት የእምነት ተቋማት ከፍ ያለ ተግዳሮት ውስጥ እንደነበሩ አመልክተው፣ ተግዳሮቶቹ በተቋማቱ ውስጥ የሰላም እጦት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል። ዘገባው የኢትዮ ፕረስ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ