አፕልን በማምረት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ጠየቁ፡፡

406
አፕልን በማምረት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) በላይ ጋይንት ወረዳ የደጋ ፍራፍሬን ማልማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በዚህም አርሶ አደሮች ውጤታማ እየሆኑ ነው። ወረዳው ለደጋ ፍራፍሬ ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው በመሆኑ ደግሞ በአፕል ልማት የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ አግዟቸዋል፡፡
በላይ ጋይንት ወረዳ የቀበሌ አራት ነዋሪ የሆኑት አብራራው ባየ እንደገለጹት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ከሰባት በላይ የአፕል ዝርያዎችን በማልማት ላይ ይገኛሉ፡፡ አፕል ለጤና ያለውን ጠቀሜታ በመረዳትም ካመረቱት አፕል ልጆቻቸውን ይመግባሉ፡፡
‹‹270 የአፕል ዛፎች አሉኝ፤ ዛፎቹ በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት ይሰጣሉ፤ አንድ ዛፍ በአማካይ 200 ፍሬ ይይዛል፤ አንድን የአፕል ፍሬ ደግሞ በአማካይ 5 ብር ይሸጣል›› ብለዋል አርሶ አደር አብራራው። በዚህ ስሌት መሠረት አርሶ አደሩ በስድስት ወር 270 ሺህ፣ በዓመት ደግሞ 540 ሺህ ብር ያገኛሉ ማለት ነው።
በላይ ጋይንት ወረዳ ቀበሌ 16 አምባ ማሪያም ነዋሪ የሆኑት ወርቁ አለባቸው እንደገለጹት ደግሞ በ1997 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት የሠጣቸውን የአፕል ችግኝ በማልማት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አትክልትና ፍራፍሬን በሰፊው ለምግብነት እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል። ከምግብነት ባለፈም ለገበያ በማቅረብ በዓመት እስከ 50 ሺህ ብር እንደሚያገኙ ነግረውናል። በዚህም ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፤ የተሻለ ኑሮም እየኖሩ እንደሆነ ነግርወናል፡፡ 500 የአፕል ችግኞችንም ለማዳቀል በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
አርሶ አደሮቹ እንደገለጹት የአፕል ምርት ትኩረት እያገኘ ቢመጣም በሚፈለገው ልክ ግን የገበያ ትስስር አለመፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
የላይ ጋይንት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ ተስፋየ መንግሥት እንደነገሩን በወረዳው ደጋማ አካባቢ 85 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር በጓሮው አፕልን ያለማል። ከዚህ በፊት ከሌላ አካባቢ ይመጣ የነበረውን የአፕል ችግኝ በወረዳው በማልማት ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨም ይገኛል ነው ያሉት። በአካባቢው እየተስፋፋ የመጣውን ባህርዛፍ በአፕል መተካት ዓላማ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በወረዳው እስከ 15 ሺህ ኩንታል የሚደርስ ምርት በዓመት እንደሚመረትም ባለሙያው ነግረውናል።
ይሁን እንጅ የገበያ ትስስር ችግር አርሶ አደሮች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዳያመርቱ እንቅፋት እንደሆነ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ወደፊት ችግሩን ለመፍታትም ከወረዳና ከዞን ንግድና ገበያ ልማት ተቋም ጋር እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው በክልሉ 6 ዞኖች በሚገኙ 11 ደጋማ ወረዳዎች አፕልን በጋራ ማልማት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች 818 ሄክታር መሬት ለምቷል፤ 21 ሺህ 300 አርሶ አደሮች ደግሞ ተሳታፊ ናቸው፡፡ በምርት ዘመኑም ከ45 ሺህ በላይ ኩንታል አፕል እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ምርቱን ከመንገድ ዳር ከመሸጥ ባለፈ በባሕር ዳር ገበያ ማዕከላት ማቅረብ መቻሉን ነግረውናል፡፡
የአፕል ልማትን ለማስፋት በዓመት ከ129 ሄክታር መሬት በላይ የአፕል ችግኝ በማልማት ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ እንደሚገኝ አቶ ይበልጣል ነግረውናል፡፡ በ2012/13 ዓ.ም የምርት ዘመንም ከ67 ሺህ በላይ ችግኞች፤ ከ4 ሺህ 300 በላይ ለሚኾኑ አባወራዎች ተሰራጭቷል፡፡ የ”ገብያ ተኮር ምርቶችን በኩታ ገጠም” ከማልማት ባለፈ ወጣቶች የአፕል ችግኝ በማልማት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ይህም ከአምስት ዓመታት በፊት ከሌላ ክልል ለአፕል ችግኝ ግዥ በየዓመቱ ይወጣ የነበረውን ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ማስቀረቱን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ለቀጣይ በጀት ዓመትም የሚተከል ችግኝ የክተባ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
የአፕል ተክል ከሁሉም የፍራፍሬ አይነቶች በተለየ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የሚመረት መሆኑ፣ ቅጠሉ ክረምት ላይ የሚረግፍ በመሆኑ በውስጡ ድንች፣ ገብስ እና ሌሎች ሰብሎች እና ቅጠላቅጠሎችን ለማምረት ተስምሚ በመሆኑ ተክሉን ምቹ እንደሚደርገው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የተሻሻሉ እና የተከተቡ ዝርያዎችን አርሶ አደሩ በስፋት እንዲጠቀም ማድርግ፣ በተመረጡ ወረዳዎች ደግሞ በአዲስ ማሰራጨት እና በፍራፍሬ ልማቱ ላይ የሚጋጥሙ ችግሮችን ከምርምር ተቋማት ጋር መፍታት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።
Next article“ያለ ሰላም ሀገር ትርጉም አልባ መሆኗን በመረዳት ሁሉም ለምርጫው ሰላማዊነት ድርሻውን ይወጣ” ኡስታዝ አቡበከር አህመድ