
<< በመገናኛ ብዙኃን የሚካሄድ ፍትሐዊ የአየር ሰዓት ምደባ ምርጫው ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የመካሄዱ አንዱ ማሳያ ነው>> የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመገናኛ ብዙኃን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ምደባ፣ በምርጫ ዘገባ፣ በመራጮች ትምህርትና በአጠቃላይ ሂደቱ የሚኖራቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል የውይይት መድረክ ከመገናኛ ብዙኃን ዴስክ መሪዎች ጋር በአዲስ አበባ እያካሄዱ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ <<ሀገራዊ ምርጫው ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የመካሄዱ ማሳያዎች አንዱ በመገናኛ ብዙኃን የሚካሄድ ፍትሐዊ የአየር ሰዓት ምደባ ነው>>ብለዋል። በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃን የምርጫ ዴስክ መሪዎች ለዚህ የሚያግዙ የሕግ ማዕቀፎችን ተረድተው እንዲሠሩ ለማድረግ ውይይቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በውይይቱ የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነምግባርና አሠራር መመሪያ እና በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምና ድልድል መመሪያ ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ- ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ