ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ፡፡

551
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ትናንት ወደ አስመራ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳይ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በውይይታቸውም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሃት የወንጀለኛ ቡድን የሕዝብን ሰላም ለማወክና ስልጣን ለመያዝ ሲል በከሸፈ ዕቅድ በሰሜን እዝ ላይ ክህደት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ ትልቁ የጦር መሣሪያ ማከማቻ በሚገኝበት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም የፌዴራል መንግሥት ሳይፈልግ ትህነግ ወደቀሰቀሰው ጦርነት መግባቱንም አስረድተዋል፡፡
ህወሃት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከመፈፀሙም በላይ በባሕር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ላይ ሮኬቶችን መተኮሱንም አስታውሰዋል፡፡ በተመሳሳይም የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ በመግባት ወደግጭት እንዲገባ ለማድረግ ወደ ኤርትራ ሮኬቶችን መተኮሱንም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ በኤርትራ እያደረጉት በሚገኙት የሥራ ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረግነው ውይይት የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል የድንበር አካባቢዎችን በአፋጣኝ ይቆጣጠራል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እና የኢኮኖሚ ትብብር ፍላጎታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
እ.ኤ.አ በ2018 የተጀመረው የሁለትዮሽ ግንኙነት በመተማመን እና በመልካም ጉርብትና መንፈስ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡ በተለይም በመተማመን ላይ የተመሰረቱ በትግራይ ክልል እና በድንበር ማዶ ባሉ ኤርትራዊያን ወገኖቻችን መካከል ያለውን ግንኙነት መመለስ አስፈላጊ ነውም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ልዩ ኀይላችን በተግባር መስዋዕትነት እየከፈለ ኢትዮጵያን ከመፍረስ እና ከመበታተን የታደገ ኃይል ነው” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኀይለማርያም
Next articleኢትዮጵያ ምን ዓይነት ምርጫ ያስፈልጋታል?