
በመራጮች ምዝገባ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነጻ የስልክ መስመር የፊታችን ሰኞ ይፋ እንደሚደረግ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫን ለማከናወን የመራጮች ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለኢቢሲ እንዳሉት የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የመራጮች ምዝገባ በምርጫ ጣቢያዎች ለሚቀጥሉት 30 ቀናት ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡
መምረጥ የሚችል ሁሉም ዜጋ የምርጫ ካርድ ከመጋቢት 16/2013 ዓ.ም ጀምሮ በማውጣት እና የመምረጥ መብቱን እንዲያረጋግጥም አሳስበዋል፡፡ በብዙ አካባቢዎች ላይም ለመራጮች ምዝገባ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በየምርጫ ጣቢያዎቹ ደርሰዋል ብለዋል የቦርዱ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ፡፡
መራጮች ለመመዝገብ የምርጫ ጣቢያዎቹ ያሉበትን አካባቢ አለመለየት፣ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን መረጃ አለማግኘት እና መራጮች ለምዝገባ ሲመጡ ችግሮች ማጋጠም ሊኖር ስለሚችል ይህን እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በኩል የፊታችን ሰኞ መጋቢት 20/2013 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጥ ነጻ የስልክ መስመር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ሶሊያና ማብራሪያ የመራጮች ምዝገባ ላይ የሚፈጠሩ ማንኛውም ችግሮች ሲኖሩ በተዘጋጀው ነጻ የስልክ መስመር በመጠቀም መራጮች በሚያደርሱት መረጃ ተንተርሶ ቦርዱ አስፈላጊውን መፍትሔ እየሰጠ ይሄዳል፡፡የመራጮች ምዝገባ ለአንድ ወር የሚቆይ በመሆኑ ወደ መጀመሪያ አካባቢ የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉ በሂደት እየተፈቱ የሚሄዱበትን እድል የሚሰጥ ነውም ብለዋል፡፡
በመላ ሀገሪቱ ድምጽ በሚሰጥባቸው 50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ከ152 ሺህ በላይ የመራጮች ምዝገባን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች እና ከ254 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች እንደሚሰማሩ ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
6ተኛው ሀገራዊ የመራጮች ምዝገባ የካቲት 22 ለማከናወን ታስቦ የነበረ ቢሆንም ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በመኖራቸው ምክንያት ቦርዱ ለመጋቢት 16/2013 ዓ.ም ማዛወሩ የሚታወስ ነው፡፡
በምስጋናው ብርሃኔ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ