“ምርጫ በሂደቱ እንጂ በውጤቱ አይለካም” የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር

155
“ምርጫ በሂደቱ እንጂ በውጤቱ አይለካም” የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) ስድስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን የምርጫ ሂደት ተግባራትን በሚገባ መከወን እንደሚገባ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምሕር ዳምጠው ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
“ምርጫ በሂደቱ እንጂ በውጤቱ አይለካም” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሂደቱ በሚገባ ከተመራ ውጤቱ ያማረ ይሆናል፤ ካልተመራ ደግሞ መጨረሻው ጥሩ አይሆንም፡፡ ለዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
በኢሕአዴግ ጊዜ ከተደረጉት አምስት ምርጫዎች በምርጫ 1997 ቅድመ ምርጫው ጥሩ ክርክር የነበረበት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተሻለ የመራጮችና የስነዜጋ ትምሕርት የሰጡበትና የመራጮችን ቀልብ የሳበ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳው ችግር ቢኖርበትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው ነው የተናገሩት፡፡
የምርጫ ሂደቱም በተለይ በከተሞች አካባቢ ግልጸኝነት ቢታይበትም ድህረ ምርጫው ችግር እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ተሞክሮም ሊወሰድ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
በስድስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ሂደት የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ምክረ ሃሳብም ሰጥተዋል፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ራሱን በአዲስ አደራጅቶ ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር እየተከተለ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን መዝኖ የሚጎድላቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረጉ፤ያሟሉትንም ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ወሳኙን የመራጮችና የስነዜጋ ትምሕርትን ማመቻቸትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ከቦርዱ የሚጠበቅ ነው፡፡
መራጮች በአግባቡ እንዲመዘገቡና የፖለቲካ ምሕዳሩ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ቦርዱ የመጨረሻውን አቅሙን መጠቀም አለበት ብለዋል፡፡ የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ግን ሊያሳስበው ይገባል ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው፡፡
ቅድመ ምርጫ አብዛኛው የምርጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወቅት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት መንቀሳቀስ ያልቻሉባቸው ክልሎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚታየውን የጸጥታ ችግር ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በትክክለኛ እውቀት እና በፓርቲዎች ትክክለኛ ፕሮግራም ላይ ተመስርቶ ድምጽ እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ከፍረጃ እንዲወጣ መሥራትም ያስፈልጋል፡፡
በምርጫ ሕጉ መሠረት ስለ ምርጫ ምንነትና ምዝገባ፣ በዕውቀት ላይ ተመስርቶ መምረጥ የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል ያለውን ዋጋ ለማሳወቅ፣ የሴቶች ተሳትፎን ለማጠናከር፣ የጸጥታ አካላትን እና የፍትሕ ተቋማትን የገለልተኝነት ደረጃ ለማሳደግ እና በምርጫ እንቅስቃሴው ሊደረጉ የሚገባቸውን ተግባራት በሚገባ ማሰልጠን ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይጠበቃል፡፡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ደግሞ የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡ የጸጥታ አካላትም የገለልተኝነት ደረጃቸውን ሊያጠነክሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ መምሕሩ እንዳሉት ፖለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ፓርቲዎች መሆን አለባቸው፡፡ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ይዘው የሚቀርቡትን አማራጭ ማሳዬት ይገባቸዋል፡፡ እንደ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ማሸነፍ የሚቻልበትን መንገድም ማሳየት አለባቸው ብለዋል፡፡
በምርጫ ሂደት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ ከተወጡ የተሻለ የምርጫ ውጤት ይኖራል፤ ጥሩ ስብጥር ያላቸው የተሻለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንዲኖር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአንድ አይነት አስተሳሰብ የሚጨበጨብበት ሳይሆን ሀሳብ በተሻለ መንገድ የሚንሸራሸርበት፣ሀሳቦችም ከግምት ውስጥ ገብተው የፖሊሲ አቅጣጫ የሚሆኑበት ዕድል እንደሚኖርም መምሕሩ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በርብ ግድብ የአሳ ምርት ላይ ያለውን ህገወጥ ሥራ በማስቆም የአሳ ምርቱን ውጤታማ ለማድረግ እየሠራሁ ነው፡፡” የደቡብ ጎንደር ዞን እንስሳት ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት
Next articleበኢትዮጵያ ከ60 ዓመታት በላይ ሲያገለግል የቆየው የንግድ ሕግ ተሻሻለ፡፡