
“የአማራ ልዩ ኃይል ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ደጀን መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ኃይል ነው” የባሕር ዳር ከተማ
አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ
ስብሰባ ላይ የአማራ ልዩ ኃይልን በተመለከተ ሁለት የምክርቤት አባላት ያነሱትን ሀሳብ በተመለከተ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች
መልእክት እያስተላለፉ ነው፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶክተር) ስለ ልዩ ኃይሉ የተነሳው ሀሳብ የተሳሳተ እና
የማይገልጸው መሆኑን ባስተላለፉት መልእክት አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው የአማራ ልዩ ኃይል “በፍትህ ከሄደች በቅሎዬ ይልቅ ያለፍትህ የሄደችው ጭብጡዬ ትቆጭኛለች” ከሚል
ሕዝብ መካከል የተገኘ መሆኑን ነው ያስረዱት። እንደ ምክትል ከንቲባው መልእክት የልዩ ኃይሉ ጀግንነትም ሆነ ጥንካሬ ሚስጥሩ
የሕዝቡ ተፈጥሯዊ ብልሀትና እውቀት ነው።
“የአማራ ልዩ ኃይል ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ደጀን መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ኃይል ነው” ብለዋል፡፡ ሥራዉና
ተግባሩም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ በመግለጽ፡፡
በመሆኑም የአማራ ልዩ ኃይልና የሚሊሺያ አባላት በሕግ ማስከበር ዘመቻም ሆነ በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በሚያጋጥሙ
የፀጥታ ችግሮች የመፍትሄ አካል ሆነው ከፊት በመሰለፍ አኩሪ ጀብድ እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕዝብንና ሀገርን በፍትሃዊነት፣ በእኩልነትና በሀቀኝነት ማገልገልን ከአባቶቹ የወረሰዉ ተፈጥሯዊ ባህርይው ነው፤ ለፍትሕና
ለእዉነት ቁሞ በከፈለዉ መስዕዋትነትም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠውን ጥቃት መክቶ ሀገርንና ሕዝብን ከብተና ታድጓል፤
ይህ ታሪክ የማይረሳው የአደባባይ ሀቅና እውነት ነው ብለዋል።
ዶክተር ድረስ ሳህሉ አንዳንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በፓርላማ ውስጥ የሚያራግቡት ሀሳብ የተላላኪነት
ሚናችውን ለመጫወት ካላቸው ፍላጉት የመነጨ እንደሆነ ነው የገለጹት። ስለ ልዩ ኃይሉ ግብረ-ገብነትና ሕዝባዊነት በሰሜኑ
የሀገራችን ክፍል በተወሰደዉ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የጁንታው ምርኮኞች በተግባር ያረጋገጡት
እውነታ ነው ብለዋል።
ዶክተር ድረስ ሳህሉ የአማራ ልዩ ኃይል የሀገር ደጀን መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ኃይል ነው ብለዋል፡፡ “ልዩ ኃይላችን ላይ
የተጀመረ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሀገርና ሕዝብ ለመበተን ቆርጠው ከተነሱ ጽፈኛ ኃይሎች የተቀዳ ስለመሆኑ ለአማራ ሕዝብ ሆነ
ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የተሰወረ አይደለም፤” ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፡፡
ዶክተር ድረስ ሳህሉ እንደገለጹት የአማራ ልዩ ኃይል ስሙ የአማራ ይሁን እንጂ ግብሩና ተግባሩ ኢትየጵያዊ ነው፤ የጁንታው
እብሪት ጫፍ ደርሶ ሀገርና ሕዝብን ለማፍረስ ሲነሳ በተጠና መልኩ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ክህደት ሲፈጽም ደርሶ
መስዋዕትነት ከፍሎ ደጀን የሆነ ኃይል ነው፡፡ በከፈለው ዋጋም የክልሉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ለደረሰበት
ደረጃ እንዲደርስ ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈጽሟል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ “ልዩ ኃይሉም ሆነ ሕዝቡ በጽፈኞች አሉባልታ ሳይገታ ለእውነተኛ ፍትሕና እኩልነት የሚያደርገው ትግል
ዛሬም እንደትናንቱ አጠናክሮ ይቀጥላል” ማለታቸውን የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር
ገጹ አስታውቋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m