የሰላም ዋጋው ስንት ነው?

1121

የሰላም ዋጋው ስንት ነው?

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) ይሄን ሰሞን ከመልካም ዜናዎች ርቀን ሰንብተናል። መርዶ መፈናቀልና የንብረት ውድመት አዘውትረን እየሰማን ነው። ከሰሞኑ እኔም መርዶዎችን ከምንሰማባቸው ቦታዎች በጥቂቶቹ እየተንቀሳቀስኩ እገኛለሁ – በዋናነት ደግሞ በአጣዬ፣ ጀውሀ፣ ሸዋሮቢትና አካባቢው። በቀጣናው የደረሰው ጠቅላላ ጉዳት እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ነጠላ ታሪኮች ደግሞ የበለጠ ልብን ይሰብራሉ።

ከክልሉ ልዩ ኃይል፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከፌደራል ፖሊስ አባላት ጋር በመሆን በአካባቢው እየተንቀሳቀስን ነው። ባልደረባዬ መላኩ የቪዲዮ ካሜራውን አነጣጥሯል። እኔ ማይክ ይዣለሁ። ጉዟችን ተጀምሯል። ከሸዋሮቢት ወደ አጣዬ መንገድ ዝግ ነው። ወደ አካባቢው ገባንና ብዙ ውድመቶችን ተመለከትን።

የሰዎች ህይወት አልፏል፤የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት ተቃጥለዋል። ዜጎች ከሞቀ ቀያቸው ተፈናቅለው ነፍሳቸውን ለማትረፍ በካምፕ ተጠልለዋል። ነፍሰጡር እናቶች በካምፕ ቀናቸውን ይቆጥራሉ፤ ህፃናት በረሃብ አለንጋ ይገረፋሉ። ከምንም በላይ ደግሞ ታመው የሚሰቃዩት ያሉበት ሁኔታ ከህሊና በላይ ነው።

ከጥቃቱ ለማምለጥ መጠለያቸውን ለቀው የወጡ ዜጎች በየማዕከሉ ተጠልለዋል። እናቶች በልጆቻቸው መራብ ፊታቸው ቅጭም ብሎ ይታያሉ። እኛም ጠጋ ብለን ማናገር ጀመርን። የተፈናቃዮች ችግር በአንደበታቸው ሲገለፅ “የሰላም ዋጋ” ፍንትው ብሎ ይታያል። በበርካታ ችግሮች ታጥረው ህይወታቸውን ለነገ ለማሳደር ተቀምጠዋል። የተገኘችዋን ፍርፋሪ ለልጆቻቸው ቆርሰው ይሰጣሉ። ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄው ሰላም ነው የሚሉት አብመድ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ቦታ ሌላ ሰብአዊ ቀውስ ከመድረሱ አስቀድሞ ወደቀያቸው መመለስ የሚችሉበትን መንገድ ማግኘት ይሻሉ። ለዚህም መንግስትን ይማፀናሉ። የሰላም ዋጋው ስንት ይሆን? ፕሮፌሰር በርናርድ የተባሉ የሥነ ልቦና ምሁር “የፍቅር መስፈሪያው ራሱ ስፍር አልባው ፍቅር ብቻ ነው” ያሉት ታወሰኝ።

የተለያዩ ሁነቶችን እያየን ከንፈራችንን ስንመጥ ቆየን። ጉዟችንም ቀጥሏል፡፡ እኔና የሥራ ባልደረባየን አልፎ አልፎ የሚሰማው የተኩስ ልውውጥ ሆዳችንን እያባባው ከቆየን በኋላ ወደ አንድ ቀበሌ አመራን።

በቀበሌው አልፎ አልፎ ጭስ ይታያል። ከኩሽና ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በቀየው የነበሩ ቤቶች ተቃጥለው ነው የሚጨሰው። ታዲያ በዚህ ቀበሌ ሌላው የተመለከትነው አሳዛኝ ነገር የአንዲት ጥጃና የአምስት ጫጩቶች ጉዳይ ነው። አካባቢው በሙሉ ተቃጥሎ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው ሄደዋል። በአራቱም አቅጣጫ ከጋራ ውጭ የሚታይ ነገር የለም። አካባቢው የተወረረ ይመስላል። የተቃጠሉት ቤቶች ረመጥ አሁንም ይጋረፋል። አልፎ አልፎ ጭስ ይታያል።

እዚህ መንደር ያገኘነው አንድ ጥጃና አምስት ጫጩቶችን ብቻ ነበር። በመንደሩ ውስጥ አንድ ጥጃና አምስት ጫጩቶች ለአንድ ሳምንት ያህል ብቻቸውን አሉ። የባለቤቶቻቸውን ድምፅ አይሰሙም። ወደ በረት መግባትና መውጣት የለም። ውሀና መኖ በወቅቱ የለም። እነሱ ግን እዚያ መንደር ባለቤቶቹ እስኪመጡ ይጠብቃሉ።

አብረውን ከነበሩ የመከላከያ አባላት አንደኛው የሚጠጣውን ውኃ በሳፋ አድርጎ ለጥጃዋ አጠጣት። ጫጩቶቹ የኛን ድምፅ ሲሰሙ ደስ ብሏቸው ሳይሆን አይቀርም ተጠጉን።

የቃጠሎውን አመድ ለብሳ ጭስ እየገረፋት በሰፈሩ ከአምስት ጫጩቶች ጋር የምትኖረው ጥጃ ማን ያውቃል እሷም ከጅብ ተርፋ ጫጩቶቹም ከጭልፊት አምልጠው በዚያ መንደር ነፍስ ዘርቶበት ይሳቅ ይጨፈርበት ይሆናል። ማን ያውቃል?

ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ – ከሸዋሮቢት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየሀገር ባለዉለታ የሆነውን የአማራ ልዩ ኀይል ስም በማጠልሸት ጁንታዉ ከመቃበር የሚነሳ የሚመስላቸዉ ተላላኪዎች ከድርጊታቸዉ ሊታቀቡ እንደሚገባ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሳሰቡ፡፡
Next article“የአማራ ልዩ ኃይል ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ደጀን መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ኃይል ነው” የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ