
የሀገር ባለዉለታ የሆነውን የአማራ ልዩ ኀይል ስም በማጠልሸት ጁንታዉ ከመቃበር የሚነሳ የሚመስላቸዉ ተላላኪዎች ከድርጊታቸዉ ሊታቀቡ እንደሚገባ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሳሰቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ባልሆኑ መድረኮች በአማራ ልዩ ኀይል ላይ የሚደረግ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተላላኪነት ካልሆነ በቀር ጁንታዉን ተመልሶ እንዲያንሰራራ እንደማያደርገዉ የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡ ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብርሃም አያሌዉ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ የጥላቻ መርዝ እንዲረጭ ያደረጉ የፓርላማ አባላት በአሠራርና ሥነ ምግባር መመሪያዉ መሰረት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።
የአማራ ልዩ ኀይል ከአማራ ክልል ሕዝቦች ተዉጣጦ ኢትዮጵያንና ሀገሩን ለመታደግ የተቋቋመ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ተናግረዋል። የጁንታዉ ቡድን ክህደት ፈጽሞ በመከላከያ ሠራዊት ላይና በአማራ ክልል ሕዝቦች ላይ በፈጸመዉ አስነዋሪ ተግባር መንግሥት ለልዩ ኀይሉ ያቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ያሳየዉ የሕግ ማስከበር ሥራ ጁንታዉን ያፈራረሰ፣ መከላከያዉን ከዳግም ጥቃት ያዳነ የብርቅዬዎች ስብስብ ነዉ።
የኢትዮጵያ ክብር ዝቅ እንዲል የሚፈልጉ የዉጭና የዉስጥ ተላላኪዎች በአማራ ልዩ ኀይል ላይ የሚያካሄዱት የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደ ብረት የሚያጠነክረዉና አንድ የሚያደርገዉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ልዩ ኀይሉ ለጁንታዉ ተላላኪዎች ጆሮ እንደማይሰጥ እና ኢትዮጵያን ለድርድር የማያቀርብ የሀገር አለኝታ መሆኑንም ነው ዋና አስተዳዳሪው ያስታወቁት።
በፓርላማ ዉሎ ትልቅ ሕዝብን ወክለዉ የተቀመጡ አካላት የፓርላማዉን የአሠራርና የሥነ ምግባር መመሪያ በመጣስ የተናገሩት የጁንታዉን “የአድርሱልኝ” የአደራ መልዕክት ብቻ ታሳቢ ያደረገ፣ ሀገርን የታደጉ ጀግኖችን ያዋረደ እኩይ ተግባር ነዉ ብለዋል። ስለሆነም እነዚህ አካላት የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር በመሞከራቸው ፓርላማዉ በአሠራሩ መሰረት በሕግ እንዲጠየቁ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
አቶ አብርሃም አያሌዉ የአማራ ልዩ ኀይል ከአማራ ሕዝብ ተዉጣጥቶ የተቋቋመ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነት እንዲጎለብት፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲጠናከር ለሰዉ ልጅ ቀድሞ የሚሞት፣ እርሱ ሞቶ ሀገር እንድትቀጥል የሚታገል የጀግኖች ስብስብ መሆኑን አስገንዝበዋል። የዚህን የሀገር ባለዉለታ በሕጋዊና ሕጋዊ ባልሆኑ መድረኮች ስም በማጠልሸት ጁንታዉ ከመቃበር የሚነሳ የሚመስላቸዉ ተላላኪዎች ከድርጊታቸዉ ሊታቀቡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ፓርላማዉ በአሠራሩ መሰረት በሕግ እንዲጠየቁ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል። ምንጭ፡ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጸሕፈት ቤት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m