
የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ቁልፍ ሚና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በብራስልስ ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ከኅብረቱ የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላየን እና ከኅብረቱ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺች ጋር ነው ውይይት ያደረጉት፡፡
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀጣይ ግንቦት ወር የምታካሂደውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደትን ጨምሮ ወቅታዊ ሀገራዊ እድገትን በተመለከተ ለኮሚሽነሮቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራን በተመለከተ እየተወሰዱ ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎችንም አስረድተል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት የልማት ትብብርን በተመለከተ ገንቢ የሚባል ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው ያስታወቀው፡፡
በውይይቱ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነሮቹ የተመዘገቡት አዎንታዊ ለውጦች እንዲቀጥሉ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በተመለከተ ለመመርመር መንግሥት ያሳየው ቁርጠኝነት እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ተሳትፈዋል የተባሉ አካላትን ለፍርድ ለማቅረብ ሥራ መጀመሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኅብረቱ ባለስልጣናት አክለውም የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያላትን ቁልፍ ሚና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተውም ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት (እ.ኤ.አ.) በ2016 ወደ ‹አውሮፓ ኅብረት-ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋርነት› መግባታቸው የሚታወስ ነው ብሏል መረጃው፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m