
በአንኮበር ወረዳ የወፍ ዋሻ ተብሎ በሚጠራው ደን ላይ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ከአቅም በላይ እንደሆነበት የወረዳው አስተዳደር ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) የወፍ ዋሻ ደን 8 ሺህ 731 ነጥብ 28 ሄክታር መሬትን የሚያካልል ሲሆን በአንኮበር ወረዳ የሚገኙ 7 ቀበሌዎችን ይሸፍናል፡፡ መጋቢት 13/2013 ዓ.ም እኩለ ቀን ጀምሮ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ የአካባቢ ነዋሪዎች ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ከመሐል ወንዝ ቀበሌ ላይ ያለው የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር የቦታው መልከዓ ምድር አቀማመጥ አስቸጋሪ እንዳደረገው አብመድ ከቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡
የመሐል ወንዝ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳኜ ብርሃኑ እንደተናገሩት መነሻውን ከግለሰብ ማሳ ያደረገውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር የአካባቢው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፤ የቦታው ገደላማ መሆን፣ ጥቅጥቅ ያለ ደን መሆኑና የእሳት ቃጠሎው እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ለመቆጣጠር ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ቃጠሎውን በፍጥነት መቆጣጠር ካልተቻለ በደኑ ውስጥ በሚገኙት የዱር እንስሳት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ በግምት ከ40 ሄክታር በላይ የደኑ ክፍል ጉዳት እንደደረሰበት የአንኮበር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አዲሱ አስጨናቂ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ ቃጠሎውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ቃጠሎው ከቀበሌውና ከወረዳ አስተዳደሩ አቅም በላይ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አየለ (ዶክተር) እንደገለጹት የእሳት አደጋው ከተነሳበት ቀን ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው የአካባቢ ጥበቃ መምሪያ በቡድን ተዋቅሮ ከአካባቢ ማኅበረሰብ ጋር የእሳት ቃጠሎን የማጥፋት ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ ሰው ተሠማርቶ እሳቱን የማጥፋት ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
ቃጠሎውን እስከ አሁን ድርስ ለመቆጣጠር ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ቦታው ተራራማና ነፋሻማ በመሆኑ እሳቱን በፍጥነት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ለፌዴራል መንግስት በማሳወቅ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችም ወደ ቦታ መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ እሳቱን ለመቆጣጠር አሁን ላይ ያለው አማራጭ የሰው ጉልበት መጠቀም ነው ያሉት ዶክተር በላይነህ የሰሜን ሸዋ ዞንና አካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ በመውጣት ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ጥብቅ ደኑን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማሳደግ ጥናት ተደርጎ ለክልል ምክር ቤት የቀረበ ነው ያሉት ዶክተር በላይነህ ሥርዓተ ምህዳርን በመጠበቅ ደኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የአካባቢው አርሶ አደሮች በነቂስ በመውጣት የእሳት ቃጠሎን ሊቆጣጠሩት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ዘገባውን ሃብታሙ ዳኛቸው እና አዳሙ ሽባባው ናቸው ያዘጋጁት፡፡
ፎቶ፡- በአንኮበር ወረዳ ኮምዩኒኬሽን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ