
የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት በተመረጡ ዞኖች እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት ከመጋቢት 17 – 20/2013 ዓ.ም በዘመቻ እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገልጿል።
በቢሮው የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ ኮምዩኒኬሽን ባለሙያ ካሳ ብርሃን ኢትዮጵያ የልጅነት ልምሻን (ፖሊዮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስወገድ በመደበኛና በዘመቻ የፖሊዮና ሌሎች የክትባት ቅኝትን በማጠናከር የማካካሻ ክትባቶችን ስትሰጥ መቆየቷን ነግረውናል።
የፖሊዮ ቫይረስ በሱዳን እና በሱማሌ ክልል በመከሰቱ ክትባቱን መስጠት አስፈልጓል ብለዋል።
የአማራ ክልልም በምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ለሱዳን ካላቸው ቅርበት በመነሳት ክትባቱን በዘመቻ መስጠት ማስፈለጉን ባለሙያው ነግረውናል።
ከሦስቱ የፖሊዮ ቫይረስ አይነቶች መካከል ፖሊዮ አይነት አንድ እና አይነት ሦስት ከመጋቢት 17 – 20/2013 ዓ.ም ቤት ለቤት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡም ማንኛውንም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ማስከተብ እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት።
የክትባቱን ተደራሽነት ለማስፋትም ከአጋር አካላት ጋር በጎንደር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃም ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ክትባቱ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ክትባትም 16 ሚሊዮን ህጻናትን ከልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) መታደግ ተችሏል። አሁን ላይ እንደ አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ የመን እና ሌሎች ሀገራት በግጭት ምክንያት ብዙ ሰዎች የሚፈናቀሉበትና ለችግር የሚጋለጡበት በመሆኑ ለቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘ መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ