በሁለተኛው ዙር መስኖ እርሻ ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

523

በሁለተኛው ዙር መስኖ እርሻ ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) በ2013 ዓ.ም በሁለተኛው ዙር በመስኖ ይለማል ተብሎ በዕቅድ ከተያዘው 108 ሺህ 422 ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 21 ሺህ 110 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

አርሶ አደር ታደሰ ውባንተ በፎገራ ወረዳ በበክስ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ታደሰ ጤፍ፣ ቲማቲም፣ ስንዴ፣ ሽንኩርት በመስኖ እያለሙ ነው፡፡

አርሶ አደር ታደሰ በዘንድሮው የመስኖ እርሻ 200 ኩንታል ምርት ለማምረት እቅድ ይዘዋል፡፡ የመስኖ እርሻ ሥራቸውን የሚያከናውኑት የወንዝ ውኃን በጄኔሬተር በመሳብ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ነዳጅ ማግኘት ግድ ይላቸዋል፡፡ ነገር ግን ነዳጅ በየጊዜው ከማደያ መጥፋት ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

በተደጋጋሚ ነዳጅ በመጥፋቱ ከግለሰቦች የሚገዙት ጥራት የሌለው ቤንዚን የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተራቸውን የቴክኒክ ችግር እንዲገጥመው ማድረጉን አርሶ አደሩ ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን ለመቀነስም የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ባደረገላቸው ድጋፍ ከባሕር ዳር ነዳጅ ማደያ ነዳጅ ለመውሰድ ወረፋ ሲጠብቁ አገኘናቸው፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ ቤንዚን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ የሚቀርብበት ሁኔታ ቢመቻች ብለዋል፡፡

አርሶ አደር ገበይ ሠጥአርገው ደራ ወረዳ ዛራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ገበይ ቃሪያ፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም በብዛት ያመርታሉ፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ካሁን ቀደም ነዳጅ በአግባቡ በመቅረቡ በትንሽ መሬት 80 ኩንታል ሽንኩርት አምርተው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ግን ከ25 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡

አርሶ አደሩ እንደተናገሩት በተለያዬ ጊዜ ነዳጅ በመጥፋቱ ከነጋዴ ላለመግዛት ባሕር ዳር ወረፋ በመጠበቅ ለእንግልት እየተዳረጉ ነው፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ቡድን መሪ አቶ ለጋስ ጀምበር በዞኑ በ2013 ዓ.ም በአንደኛ ዙር በመስኖ እርሻ 30 ሺህ 651 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን ነግረውናል፡፡

አቶ ለጋስ በሁሉም ወረዳዎች የመስኖ የንቅናቄ መድረክ በመፈጠር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ አርሶ አደሮች በመስመር እንዲዘሩ፣ ሣይንሳዊውን መንገድ ተከትለው ግብዓትና ምርጥ ዘር እንዲጠቀሙ ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን በመስኖ ልማት ሥራ

 እስካሁን 30 ሺህ 761 ሄክታር መሬት በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት በዘር ተሸፍኗል

 45 ሺህ 975 ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል

 ከ160 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

 20 ሺህ ኩንታል የተሻሻሉ የአትክልት፣ የአዝዕርትና የሥራስር ምርጥ ዘሮችን ለመጠቀም ታቅዶ 14 ሺህ 975 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል

 መስኖን ለማዘመን በተደረገው ርብርብ ተገድበው ጥቅም ከሚሰጡ ወንዞች በተጨማሪ 6 ሺህ 550 የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል

 በሁለተኛው ዙር መስኖ እርሻ 14 ሺህ 18 ሄክታር መሬት ይለማል ተብሎ በዕቅድ ተይዞ እስካሁን 5 ሺህ 860 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ከዞኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ አወቀ ዘላለም የዘንድሮውን የመስኖ ልማት ሥራ በውጤት ለማጠናቀቅ በሁሉም ዞኖች ለባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች ሥልጠና በመስጠት መጀመሩን ነግረውናል፡፡ በዚህም በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር መስኖ 248 ሺህ 40 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ37 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል ብለዋል፡፡

እስካሁንም በአንደኛ ዙር 226 ሺህ 714 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሠብሠብ መቻሉን ነግረውናል፡፡
በመስኖ እርሻ ሥራው ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ናቸው ብለዋል፡፡

275 ሺህ 530 ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አቶ አወቀ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በርካታ የውኃ አማራጮች ጥቅም እየሰጡ ነው ያሉት ባለሙያው 27 ሺህ 723 የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ በሁለተኛው ዙር መስኖ በዘር ይሸፈናል ተብሎ በእቅድ ከተያዘው 108 ሺህ 422 ሄክታር መሬት እስካሁን 21 ሺህ 110 ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል፡፡

ከእቅድ አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው የመስኖ እርሻው የመኸር እርሻውን እንዳይጋፋ መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ሁሉም የመስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደር ማሳውን በዘር መሸፈን እንዲችል እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የዋጋ ውድነት ለማስታገስ ድንች ደቡብ ሜጫ፣ ሠከላ፣ ደጋ ዳሞት እና ቋሪት፤ ቲማቲም ምዕራብ ደንቢያ፣ ላይ አርማጭሆ፣ ጣቁሳ እና ጭልጋ ወረዳዎች ላይ ለማምረት እየተሠራ መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የተከሰተው የቤንዚን እጥረት በመስኖ እርሻው ምርት ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የግብርና ቢሮ ከንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር አርሶ አደሮች ቤንዚን የሚያገኙበትን መንገድ አመቻችተናል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች በመስኖ የሚያለሙት ሠብል ለብልሽት እንዳይጋለጥ የወሰዱትን ስልጠና እና የባለሙያ ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየተቀናጀ የመከላከል ሥራ በመሥራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን መከላከል እንደሚገባ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleየጸጥታ ችግር የተፈጠረባቸው የሰሜን ሸዋ ዞንና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዳራቸው ሰላማዊ መሆኑን አስተዳደሮቹ ገለፁ፡፡