
የተቀናጀ የመከላከል ሥራ በመሥራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን መከላከል እንደሚገባ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የተቀናጀ ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን እና የማስጀመሪያ ክትባት መሰጠቱን አውስተዋል፡፡
አቶ ወርቅነህ እንዳሉት የዓለም ጤና ድርጅት ባደረገው ድልድል ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶዝ (አስትራዜኒካ) የተባለው ክትባት ወደ ሀገሪቱ ገብቷል፡፡ በቀጣዩ ግንቦት ወር ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዶዝ ወደ ሀገሪቱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን ክትባት ለተጠቃሚው ለመስጠትም ለባለሙያዎች በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየደረጃው ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና የሥራ ኀላፊዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
አቶ ወርቅነህ እንዳስታወቁት በመጀመሪያው ዙር ክትባቱን የሚወስዱ በጤና ተቋማት የሚሠሩ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፤ በአማራ ክልል እስካሁንም 80 ሺህ ሰዎችን በመመዝገብ ለፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃው ተልኳል፤ ያልተመዘገቡ የጤና ባለሙያዎችና በጤና ተቋም የሚሠሩ ካሉም እንዲመዘገቡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለጻ በቀጣዩ ዙር እድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆናቸውና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ክትባቱን ያገኛሉ፡፡ የተጋላጭነት መጠን እየታዬ ለሁሉም እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እያስከተለ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ያደጉ ሀገራትም ክትባቱን ለዜጎቻቸው እየሰጡ ነው፡፡ እንደ አስተባባሪው መልዕክት ችግሩን ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም ክትባት አንዱ መንገድ በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ክትባቱን በመውሰድ በሽታውን ለማስቆም በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡
አቶ ወርቅነህ ክትባቱ በተወሰደ ጊዜ እንደማንኛውም ክትባት ትኩሳት እና ሌሎች ምልክቶች ሊኖሩት ስለሚችሉ መደናገጥና ሌላ ጭንቀት ውስጥ መገባት የለብንም ነው ያሉት፡፡
“ክትባቱ የደም መርጋት ችግር ያመጣል” የሚል ሀሳብ እንደሚነሳ ጥያቄ የቀረበላቸው አስተባባሪው የዓለም ጤና ድርጅት አረጋግጦ ያሰራጨው በመሆኑ ማኅበረሰቡ ብዥታውን ማስወገድ አለበት ብለዋል፤ በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር መውሰድ ጠቃሚ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ክትባቱን በአንድ ጊዜ ለሁሉም ዜጎች ማድረስ ሥለማይቻል አሁን በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ እጅን በአግባቡ መታጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛን በአግባቡ መጠቀም፣ ርቀትን መጠበቅና ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም ስርጭቱን መከላከል ተገቢ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ