“የታጠቁ ቡድኖች የመንግሥትን የፀጥታ መዋቅር መገዳደር የሚያስችላቸውን ኀይል የት አገኙ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡” መርሐጽድቅ መኮንን

249
“የታጠቁ ቡድኖች የመንግሥትን የፀጥታ መዋቅር መገዳደር የሚያስችላቸውን ኀይል የት አገኙ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡” መርሐጽድቅ መኮንን
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት በአማራ ክልል ውስጥ ከተፈጠሩ የፀጥታ ስጋቶች መካከል በሰሜን ሽዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች መካከል የተፈጠረው ችግር አንዱ ነበር፡፡ በወቅቱ በሰው ህይዎት እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሶ ያለፈውን ያንን የፀጥታ ችግር ኃላፊነቱን በግልፅ የወሰደ ኃይል ባለመኖሩ ችግሩ የታጠቁ ኃይሎች የፈጠሩት ችግር ነው በሚል ብቻ ተዳፍኖ መቅረቱ ይታዎሳል፡፡
የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለማርገብ በወሰደው መጠነ ሰፊ እርምጃ ላለፉት ሁለት ዓመታት አንፃራዊ ሰላም ቢታይም ችግሩ ከመሰረቱ ግን የጠፋ አልነበረም፡፡ በአካባቢው የነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ልዩ ኀይል አባላት ለነበረው አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት ሚናቸው የጎላም ነበር፡፡
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ህገ-ወጡ የህወሐት ቡድን በሀገር ላይ የቃጣውን ትንኮሳ ተከትሎ በዚህ አካባቢ የነበረው የመከላከያ ኀይል ለግዳጅ ወደ ሌላ አካባቢ ተንቀሳቀሰ፡፡ በዚህ ወቅት በሰሜን ሽዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አካባቢዎች ቀድሞ የነበረው የፀጥታ ችግር ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት ቢኖርም የአማራ ልዩ ኀይል በአካባቢው በመኖሩ ችግር ሳይፈጠር እንዲቆይ አግዟል፡፡
ከሰሞኑ በአካባቢው የነበረው የአማራ ልዩ ኀይል ለሌላ ግዳጅ አካባቢውን ለቆ መንቀሳቀሱን ተከትሎ የፀጥታ ችግሩ ሊያገረሽ ይችላል የሚል የሕዝብ ስጋት ቢኖሩም ስጋቱን መሰረት ተደርጎ አፋጣኝ ምላሽ ባለመወሰዱ ስጋቱ እውን ሆኖ በአካባቢው ውጥረት ተፈጥሯል፡፡ በአካባቢው የቡድን መሳሪያዎችን የታጠቁ የሽብር ቡድኖች በሌሊት ወደ ሰሜን ሽዋ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች በመዝለቅ በሰው ህይዎት እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ችግሩን ለመቆጣጠር ወደ አካባቢው የፌዴራል ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ ኀይሎች ቢገቡም ውጥረቱ ግን በቀላሉ ሊረግብ አለመቻሉን መዘገባችን ይታወቃል፡፡
የፀጥታ ስጋት መኖሩ በሕዝብ እየተነገረ ቀድሞ መድረስ ያልተቻለው እና የሕግ የበላይነትን በዘላቂነት ለመፍታት ያልተቻለበት ምክንያ ምንድን ነው? ስንል የርዕሰ መስተዳድሩን የሕግ ጉዳይ አማካሪ አቶ መርሐፅድቅ መኮንንን አነጋግረናቸዋል፡፡
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሀገር ደረጃ የፀጥታ ችግር ሲፈጠር እሳት ለማጥፋት የሚደረገውን ርብርብ ያክል ቀድሞ ለመከላከል የሚደረገው የመረጃ እና ደኀንነት ሥራ ደካማ ነው የሚሉት አቶ መርሐጸድቅ መኮንን ሕዝቡ ለመንግሥት ቀድሞ ስጋቱን ሲናገር እንኳን መፍትሄ አልተወሰደም ነበር ነው ያሉት፡፡ በቅርብ ርቀት የአካባቢውን ሰላም ለማናጋት የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች መኖራቸው ይታመናልም ነው ያሉት፡፡ ችግሩ “ጭር ሲል አልወድም” የሚል የድብብቆሽ ጨዋታ የሚጫዎቱ ኀይሎች ተጠራርተው የፈጠሩት ነው የሚሉት አቶ መርሐጸድቅ በአካባቢው የነበረው የአማራ ልዩ ኀይል ለሌላ ግዳጅ አካባቢውን ሲለቅ ተጠብቆ መፈፀሙ የክልሉን ሰላም በተጠና ሁኔታ ለማናጋት የሚሰሩ ኀይሎች ሙሉ በሙሉ አለመጥፋታቸውን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡
እንደ አቶ መርሐጸድቅ ገለፃ በአሁኑ ጊዜ አነሰም በዛም አንፃራዊ ሰላም ካለባቸው ክልሎች አንዱ የአማራ ክልል ነው፡፡ የሰሞኑ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሽዋ ዞን አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችም የክልሉን ሰላም በመረበሽ መጭው ሀገራዊ ምርጫ ስጋት ላይ እንዲወድቅ ታልሞ የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት በሚል እሳቤ በየትኛውም አካባቢ ሰርቶ ሀገሩን እና ራሱን ለመለወጥ እየሠራ ቢሆንም የህይዎት ዋጋ እየከፈለ መሆኑን አውስተው ሰሞኑን በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከክልሉ ውጭ የሚሳደደውን አማራ በሆደ ሰፊነት ባሳለፈ ማግሥት የተፈጸመ ነው ብለዋል፡፡
“የታጠቁ ቡድኖች የመንግሥትን የፀጥታ መዋቅር መገዳደር የሚያስችላቸውን ኃይል የት አገኙ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል” የሚሉት የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ ጉዳይ አማካሪ የብልጽግና አመራሮች በጋራ ቁጭ ብለው ሊገመግሙ ይገባል ብለዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የቡድን መሳሪያ የታጠቀ ሽፍታ፣ ለመንግሥት የፀጥታ ኀይል ፈታኝ የሆነ ቡድን እና የሀገር ስጋት የሆነ አካል በመንግሥት ውስጥ ሆኖ ከጀርባው መረጃ የሚያደርሰው፣ የሚያስታጥቀው እና የሚደግፈው አካል ላለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ነው ያሉት፡፡ ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለም ሕዝብ በመንግሥት የፀጥታ ተቋማት ላይ እምነት አጥቶ ራሱን ለመከላከል ይገደዳል የሚሉት አቶ መርሐጽድቅ ይህ ደግሞ ለርስ በዕረስ ግጭት ስለሚያጋልጥ አሰፈላጊው ትኩረት ከክልል እና ከፌደራል መንግሥት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአማራና የኦሮሞ ህዝብ አንድ ነው” የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
Next articleʺሕይወቱን የሰጠላት ሀገር ለሐውልቱ መቆሚያ ስፍራ ነፈገችው”