“ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት የለውም፤ እኛን እየወጋን ያለው የተቀናጀ፣ የታጠቀና የተደራጀ ኀይል ነው” የቀወት ወረዳ ነዋሪዎች

334

“ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት የለውም፤ እኛን እየወጋን ያለው የተቀናጀ፣ የታጠቀና የተደራጀ ኀይል ነው”
የቀወት ወረዳ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ አስተዳደርና አጎራባች አካባቢዎች እየደረሰ
ያለው ጥቃት አሁንም አልቆመም። በተደራጀ መንገድ ጥቃት እየፈፀመ የሚገኘው ታጣቂ ቡድን የታጠቀው ከባድ መሳሪያ በመሆኑ
እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ነው በሸዋሮቢትና ቀወት ወረዳ የሚኖሩ ሰዎች የተናገሩት።
“ማን እያጠቃን እንደሆነ እንኳን ግራ እየገባን ነው፤ ምክንያቱም ጥቃት አድራሹ ኀይል የሚተኩሰው ጦር መሳሪያ በግለሰብ እጅ
ስለማይያዝ ነው፤ አሁንም ጥቃቱን ማስቆም አልተቻለም” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
አሁንም ቢሆን ከሸዋሮቢት ወጣ ብለው በሚገኙ ጀውሃ፣ ነጌሶ፣ ኩሪብሪና ሞላሌ በተባሉ አካባቢዎች ጥቃት ተፈፅሟል ብለዋል።
አብመድ የጠየቃቸው የነጌሶ ቀበሌ ነዋሪው እሸቴ ደለለኝ እንደተናገሩት በተሰነዘረው ጥቃት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም
ወድሟል። ከረፋዱ 5:00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ጥቃቱ የተፈፀመ ሲሆን ከፍተኛ ቃጠሎ በማስነሳት የዜጎች ሀብትና ንብረት
በታጣቂው ኀይል ውድመት ደርሶበታል ብለዋል።
የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ለማስመሰል የሚደረግ ጥረት እንዳለ የገለፁልን የቀወት ወረዳ የሕዝብ ሰላምና ደኀንነት ጽሕፈት
ቤት ኀላፊ አቶ ውብሸት አያሌው ይሄ ፈፅሞ የተሳሳተ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ልዩ ኀይልን በተመለከተ ዛሬ በነበረው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተነገረው የበሬ ወለደ ተረት ተረት ነው ብለዋል። ንጹሃን
እየተገደሉ ነው ያሉት ኀላፊው ህዝቡ እንደ ህዝብ አብሮ የኖረ እየኖረ ያለ ነው ብለዋል። ልዩ ኀይሉም ቢሆን ለሰላም ዋጋ
የሚከፍል እንጂ በተገለፀው ልክ የሞራል ውድቀት ውስጥ የገባና የሚገባ አይደለም ነው ያሉት። ለሰላም ሁላችንም ካልተባበርን
የሚደርሰው እልቂት ይከፋል ብለዋል።
የጥፋት ኀይሉ ወደ ሸዋሮቢት በመግባት ጥፋት እንዳይፈፅም ኀብረተሰቡን አስተባብረን ነው እየተከላከልን ያለነው ብለዋል። እንደ
ሕዝብም እንደ ክልልም የአማራ ክልል ከሀገሪቱ ክልሎች በተለየ መንገድ የዜጎችን መብት ያከበረ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ኤሊያስ ፈጠነ – ከሸዋሮቢት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአንዳንድ እንደራሴዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች በምክር ቤት አባላት የአሠራር እና ሥነ ምግባር ደንብ የተከለከሉ መሆኑን ያናገርናቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ገለጹ፡፡
Next article“እርስ በርስ ከተደጋገፍን በቱሪዝም ዘርፍ ተዓምር መሥራት ይቻለናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ