
አንዳንድ እንደራሴዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች በምክር ቤት አባላት የአሠራር እና ሥነ ምግባር ደንብ የተከለከሉ መሆኑን ያናገርናቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተካሂዷል፡፡
ውይይቱ ቀደም ተብሎ መርሃ ግብር የተዘጋጀለት እና የምክር ቤቱ አባላትም ግልጽ ያልሆነላቸውን ጥያቄ ያቀረቡበት ነበር ተብሏል፡፡ ነገር ግን ከመደበኛው ጥያቄ በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባላት የግል ስሜታቸው የተንፀባረቀበት፣ ብቁ መረጃ ያልተያዘበት፣ የአንድን ማኅበረሰብ ማኅበረሰባዊ ስሪት ያጎደፈ፣ ለዘመናት ተቻችለው እና ተከባብረው በኖሩ ሐይማኖቶች መካከል ቁጣን የሚቀሰቅስ እና ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ ጥያቄ እና አስተያየት ሲሰነዘር ተስተውሏል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል በችግር ጊዜ የተፈተነ፣ በሕግ ማስከበር ዘመቻው የህይዎት መስዋእትነት ለመክፈል ያላመነታ፣ ክልሉንና ሀገሩን በቅንነት ያገለገለ እና እያገለገለ ያለ የፀጥታ ተቋም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለአበርክቶው በማይመጥን፣ የባዕዳን መሰረተ ቢስ ውንጀላን ተቋቁሞ ዛሬም እንደትናንቱ ሀገርና ሕዝብን በቁርጠኝነት ቀን ከሌሊት በሚያገለግልበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ዝናን የሚያጎድፍ ትችት እና ወቀሳ ከአንዳንድ የምክር ቤት አባላት አስተናግዷል፡፡
ለመሆኑ የዛሬውን የፓርላማ አንዳንድ ንግግሮች አባላቱ እንዴት አይተዋቸው ይሆን? የምክር ቤቱ አባላት የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ውጤቱ ሕዝብን ከሕዝብ እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ ንግግር እንዴት ያስተናግዳል? ስንል ከአንድ የምክር ቤት አባል ጋር የስልክ ቆይታ አደረግን፡፡
በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሰረት በፓርላማው ለማብራሪያ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ቀድመው እንዲደርሱ ይደረጋል ያሉን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በፓርላማው ረዳት የመንግሥት ተጠሪ የተከበሩ አቶ ጫኔ ሽመካ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ጫኔ ገለፃ የዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ በ10 ዓመቱ የልማት ፍኖተ ብልፅግና ላይ ተወያይቶ ለማፅደቅ የአባላት ጥያቄዎች የደረሱት እና መርሃ ግብሩ የተዘጋጀመው ቀደም ብሎ ነበር፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዙሪያ በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄው መነሳቱ በመርሃ ግብሩ የተያዘ ባይሆንም ክፋት አልነበረውም ብለዋል የተከበሩ አቶ ጫኔ፡፡ መሰረታዊ ችግሩ ጥያቄዎቹ እና አስተያየቶቹ በምክር ቤቱ አባላት የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሰረት የተከለከሉ መሆናቸው ነው ይላሉ፡፡
ውጤታቸው ብሔርን ከብሔር እንዲሁም ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተሰንዝረዋል ነው ያሉት አቶ ጫኔ፡፡ የምክር ቤት አባላቱ የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ስለማይፈቅድ፣ የወከሉትን ማኅበረሰብ የሞራል ልዕልና መላበስ ግድ ስለሚል እና በቂና አጥጋቢ ምላሽ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተሰጠ እንጂ የተነሱት ጥያቄዎች መሰረታዊ የአካሂድ ዝንፈት እና ህጋዊ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ነበሩ ብለዋል፡፡
አቶ ጫኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡበት መንገድም በሳል እና የጥያቄውን መሰረተ ቢስነት ያመላከተ ነበርም ብለዋል፡፡ የአንድ ሀገር ከፍተኛው የስልጣን ባለቤት በሆነ እንደራሴ ለዘመናት ተዋልዶ እና ተዋዶ የኖረን ሕዝብ ለግጭት በሚያነሳሳ እና ሃይማኖታዊ ቁጣን ሊቀሰቅስ በሚችል መልኩ ጥያቄ መቅረቡ ተመልካቹን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የምክር ቤት አባላቱንም ያሳዘነ ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን የተከበሩ አቶ ጫኔ በእንደራሴዎቹ ከተነሳው ሃሳብ ይልቅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ምላሽ ሚዛን የደፋ መሆኑ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ