መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ተመን ባወጣባቸው የግብርና ምርቶች ላይ ቀጣይነት ያለው ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ሸማቾች ተናገሩ፡፡

325
መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ተመን ባወጣባቸው የግብርና ምርቶች ላይ ቀጣይነት ያለው ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ሸማቾች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን አውጥቶ ተፈፃሚ እንዲሆን እየሠራ ነው። ቢሮው የኑሮ ውድነትን እያባባሱ ነው ባላቸው ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸዉን የግብርና ምርቶች ላይ በጥናት የተደገፈ የዋጋ ተመን በማውጣት ገበያዉን ለማረጋጋት እየሠራ መሆኑን አመላክቷል፡፡
አቶ ዓለምነው ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ የአዲስ ዓለም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ዓለምነው በወጣው የዋጋ ተመን መሠረት በርበሬ ለመግዛት መውጣታቸውን ነው የነገሩን፡፡ “ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ያወጣው የዋጋ ተመን ሸማቹንም ሆነ ነጋዴዉን የማይጎዳ ነው ብለዋል፤ የወር ገቢያቸው 800 ብር እንደሆነ የነገሩን አቶ ዓለምነው ተመን ከመውጣቱ በፊት በነበረው 210 ብር ለመግዛት እንደማይችሉ ነግረውናል፤ አሁን በወጣው ተመን አንድ ኪሎ በርበሬ 140 ብር መሆኑ ተመጣጣኝ ነውም ብለዋል፡፡
መንግሥት ተመኑ ተፈፃሚ እንዲሆን ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለበት የሚሉት አቶ ዓለምነው የንግዱ ማኅበረሰብም በወጣው የዋጋ ተመን መሠረት ጥራት ያላቸውን ምርቶችን እንዲያቀርብም ጠይቀዋል፡፡
በወጣው የዋጋ ተመን ተጠቃሚ ለመሆን መውጣታቸው የተናገሩት ወይዘሮ ሰናይት ውቤ በወጣው የዋጋ ተመን ተጠቃሚ ለመሆን ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሸማቾች በርበሬ ለመግዛት ወረፋ በመያዝ እየተጉላሉ ነው፡፡ የማኅበረሱን እንግልት ለመቀነስ ሁሉም ነጋዴዎች በተመኑ መሠረት ምርት እንዲያቀርቡ ቢደረግ ብለዋል፡፡
ከንግዱ ማኅበረሰብ አንዱ የሆኑት በለጠ መንግሥቴ፣ መንግሥት የተመነው ዋጋ ነጋዴውን የሚጎዳ ነው ብለዋል። “ዛሬ 1 ኪሎ በርበሬ በ140 ብር እንድሸጥ ተደርጓል፣ እኔ ግን በ 190 ብር እና በ200 ብር ነው የገዛሁት፣ ይህ ፍትሐዊነት የለውም” ነው ያሉት፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተስፋዬ ታደሠ ከመጋቢት 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ በአራት የግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን ወጥቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡
በወጣው የዋጋ ተመን መሠረት ነጭ ጤፍ በኩንታል 3 ሺህ 917 ብር፣ ሠርገኛ ጤፍ በኩንታል 3 ሺህ 559 ብር፣ ነጭ በቆሎ በኩንታል 1 ሺህ 225 ብር እንዲሁም በርበሬ (አንደኛ ደረጃ) በኪሎግራም 139 ብር ከ 34 ሣንቲም መሆናቸዉን አስገንዝበዋል፡፡ ከመጋቢት 13/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተመኑ በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበርና በሁሉም ነጋዴዎች ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ ከተመኑ ውጪ የሚያከማች ወይም የሚሸጥ ነጋዴ ካየ ወይም ከሰማ ጥቆማ ሊያደርሳቸው እንደሚችል አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል። ተመኑ ከወጣ ጀምሮ በአንዳንድ ምርቶች ላይ የበለጠ የዋጋ መቀነስ እንደተስተዋለም ኃላፊው ተናግረዋል።
የዋጋ ተመን ከመውጣቱ በፊት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት መደረጉንም አስታውሰዋል። የዋጋ ተመኑን የሚቆጣጠር ግብረኃይል ስለተቋቋመ ተመኑን ጥሶ የተገኘ ነጋዴ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድበትም ነው አቶ ተስፋዬ የገለጹት።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተዋቸው ወርቁ ገበያዉን ለማረጋጋት የወጣው የዋጋ ተመን ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በቅርቡ ስለሆነ ገና በሚፈለገው ልክ ለውጥ አልመጣም ብለዋል። እስከ አሁን በተሠራው ሥራ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እየተቆጣጠሩ እንደሆነ አቶ ተዋቸው አስረድተዋል።
ያለ ፈቃድ የሚሠሩ፣ ለገበያው ማቅረብ ሲጠበቅባቸው ምርቱን አከማችተው የተያዙ እና ከተገቢ ዋጋ በላይ ሲሸጡ በተገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ እርምጃዎች ተወስዷል ብለዋል። በክልሉ እስከ አሁን በተወሰደው እርምጃ ከ3 ሺህ 200 በላይ ድርጅቶች ታሽገዋል፣ 6ሺህ ኩንታል የሚሆን ጤፍ ተከዝኖ በመገኘቱ በቀጣይ ለማኅበረሰቡ ለማከፋፈል መታቀዱን እና ተከዝነው የተገኙ ሌሎች ምርቶችም መኖራቸውን አስረድተዋል።
“ዛሬ ኅብረተሰቡ እየገዛ የሚገኘው በርበሬ ከሦስት ወራት በፊት የተገዛ ነው፤ ምናልባትም በኪሎ ከ 100 ብር ወይም ከዚያ በታች ነው ገዝተው ያከማቹት፤ አንዳንድ ነጋዴዎች በተመጣጣኝ ትርፍ መሸጥ ሲገባቸው በመመሳጠር አላስፈላጊ የዋጋ ንረት ሲፈጥሩ ተስተውለዋል” ያሉት ምክትል ኃላፊው የዋጋ ተመኑ ከሸማቹ የበለጠ የነጋዴዉን ተጠቃሚነት ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአማራ ልዩ ኃይል በሕግ ማስከበር ዘመቻው መሬቴን ላስመልስ ብሎ ተደራጅቶ ወደ ዘመቻው እንደገባ የሚያስመስሉ አሉ፣ ይህ ስህተት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር)
Next articleአንዳንድ እንደራሴዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች በምክር ቤት አባላት የአሠራር እና ሥነ ምግባር ደንብ የተከለከሉ መሆኑን ያናገርናቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ገለጹ፡፡