
“የአማራ ልዩ ኃይል በሕግ ማስከበር ዘመቻው መሬቴን ላስመልስ ብሎ ተደራጅቶ ወደ ዘመቻው እንደገባ የሚያስመስሉ አሉ፣ ይህ ስህተት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር)
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ላይ የምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
ከምክር ቤት አባላቱም “የአማራ ልዩ ኀይል በአካባቢው በሚኖሩ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል” ብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረቡ አባላት ነበሩ፡፡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ችግሩ የሕዝብ እና የልዩ ኀይል ሳይሆን ችግር በማራገብ እንጀራ የሚጋግሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ነው ብለዋል፡፡
“ሕዝቡ እኛ ከመፈጠራችን በፊትም ተዋዶ እና ተዋልዶ አብሮ” ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሹመኛ እስከ ፖለቲከኛ፣ ከምክር ቤት ጠያቂ እስከ ማኅበረሰብ አንቂ ጉዳዩን አታጋግሉት የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ልዩ ኃይል የራሱን ሕዝብ አይጨፈጭፍም” የሚል ምላሽም ሰጥተዋል፡፡
“የአማራ ልዩ ኃይል በሕግ ማስከበር ዘመቻው መሬቴን ላስመልስ ብሎ ተደራጅቶ ወደ ዘመቻው እንደገባ የሚያስመስሉ አሉ፣ ይህ ስህተት ነው” ብለዋል፡፡ ሶሮቃና ቅራቅር ላይ ጦርነቱን የጀመረው አማራ ልዩ ኃይል አይደለም፤ ልዩ ኃይሉ ባሕርዳር ተቀምጦ ነው ጦርነት የተከፈተበት ነው ያሉት፡፡ ሀገር እየጠበቀ ያለው መንግሥት የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል ከሌላ ቦታ እንደመጣ አድርጎ መሳል ተገቢ እንዳልሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ከፈለገው የትኛውም ቦታ ላይ ማሰማራት ይችላል ነው ያሉት፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ