
ከሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን መመገብ እንደታቸለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) በትግራይ ክልል ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ ከ92 በላይ የእርዳታ ማከፋፋያ ቦታዎችን በማዘጋጀት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን መመገብ እንደተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡ ይህም የሀገርን አቅም ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በእርዳታውም መንግሥት 70 በመቶ የዕለት ደራሽ ምግብ እያቀረበ ነው ብለዋል፡፡ ከዕለት ደራሽ ምግብ በተጨማሪ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በትግራይ ክልል መሰረተ ልማት ጥገና ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ከውጭ ሀገር በእርዳታ የሚመጣ ምንም ምግብም እንዳልተመለሰም አስታውቀዋል፡፡
ትህነግ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የትግራይ ሕዝብ በሴፍቲኔት ሲረዳ መቆየቱንም ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአምበጣ መንጋና ሕግ ማስከበር ዘመቻው ተጨምሮበት ዜጎችን ለችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ካለበት ችግር እንዲወጣም መንግሥት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም በሁሉም ወረዳና ዞኖች ሥርዓት ዘርጎቶ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ሕዝቡ፣ የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች መተጋገዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ በአግባቡ እንዳይደርስ የትህነግ ርዝራዦች ችግር እየፈጠሩ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር ተባባሪ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ27 ሀገራት የተውጣጡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ